ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ለስታርት አፕ ልዩ ትኩረት መሰጠቱና ምቹ ሁኔታ መፈጠሩም የሚደነቅ ነው

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 7/2016(ኢዜአ)፡-በኢትዮጵያ ለስታርት አፕ ልዩ ትኩረት መሰጠቱና ምቹ ሁኔታ መፈጠሩም የሚደነቅ መሆኑ ተገለጸ።

በሳይንስ ሙዚየም ከመጋቢት 30 እስከ ሚያዝያ 20 ቀን 2016 ዓ.ም የሚቆየው የኢትዮጵያ "ስታርት አፕ" አውደ-ርዕይ አንድ ሳምንት ሆኖታል።

የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በይፋ የተከፈተው አውደ-ርዕይ የተለያዩ የፈጠራ ሥራዎች ቀርበውበታል።

በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ በግብርና፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በኢንዱስትሪ፣ በፋይናንስና በሌሎች ዘርፎች የተሰሩ የፈጠራ ውጤቶችም ይጠቀሳሉ።

አውደ-ርዕዩን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ ምሁራን፣ ተማሪዎችና ሌሎችም የኅብረተሰብ ክፍሎች ጎብኝተውታል።

ከአውደ-ርዕዩ ጉብኝት በተጓዳኝ አውደ-ጥናቶች እየተካሄዱ ሲሆን፤ በዛሬው እለትም ከጉዳዩ ጋር የተገናኘ መድረክ ተካሂዷል።

በዚህም ኢኖቬቲቭ ፋይናንስ ላብ፣ የኢትዮጵያ የስታርት አፕ  ማኅበር እና የኢትዮጵያ የውጭ አገልግሎት ማኅበር በሚመለከት ጽሑፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጓል።

በመድረኩ የተገኙት የአፍሪኮም ቴክኖሎጂስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር መሥራች ባህሩ ዘይኑ፤ በኢትዮጵያ ለስታርት አፕ ልዩ ትኩረት መሰጠቱና ምቹ ሁኔታ መፈጠሩንም አድንቀዋል።

የአንድ ሀገር እድገት እና ብልፅግና መሠረት የሚያደርገው ጥራት ባለው ስታርት አፕ በመሆኑ በትኩረት መሥራት ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የስታርት አፕ ማኅበር ሰብሳቢ ነብዩ ይርጋ፤ በኢትዮጵያ ያለውን የስታርት አፕ እድገት እና ልማት ለማጎልበት ማኅበሩ የሚሰራ መሆኑን ገልፀዋል።


 

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ ለስታርት አፕ የፖሊሲ ማዕቀፍ ማዘጋጀትን ጨምሮ ምቹ ሁኔታዎች እየተፈጠሩ መሆኑን አንስተው፤ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠቁመዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም