በአማራ ክልል''በኢትዮጵያ ታምርት" ንቅናቄ ውጤት እየተመዘገበ ነው - የክልሉ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል''በኢትዮጵያ ታምርት" ንቅናቄ ውጤት እየተመዘገበ ነው - የክልሉ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ
ደሴ፤ ሚያዚያ 7/2016(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል ''በኢትዮጵያ ታምርት" ንቅናቄ በተከናወኑ ተግባራት ተስፋ ሰጪ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን የክልሉ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ አስታወቀ።
የደቡብ ወሎ ዞን ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ከባለሃብቶችና ባለድርሻ አካላት ጋር በቃሉ ወረዳ የምክክር መድረክ አካሂዷል።
በምክክር መድረኩ የተገኙት የቢሮው ሃላፊ አቶ እንድሪስ አብዱ እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የክልሉን የኢንቨስትመንት ዘርፍ በማነቃቃት ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል።
በተለይም በዘርፉ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን በመፍታት፣ ቅንጅታዊ አሰራርን በማሳደግ፣ ምርታማነትን በማጎልበት፣ ተኪ ምርት በማምረትና የውጭ ምንዛሬ በማምጣት የተሻለ ውጤት መመዝገቡን ተናግረዋል።
በንቅናቄው ባለፉት ሁለት ዓመታት በችግር ውስጥ የቆዩ 255 ፋብሪካዎች ወደ ስራ እንዲገቡ ከማድረግ ባሻገር ለ63 ሺህ ዜጎች ቋሚ የስራ እድል እንዲፈጠር ማስቻሉን ገልጸዋል።
ባለፉት ዘጠኝ ወራት በተከናወነ እንቅስቃሴም 276 ቢሊዮን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ 1 ሺህ 885 ባለሃብቶች አዲስ የኢንቨስትመንት ፈቃድ መሰጠቱን አመልክተዋል።
ከውጭ የሚመጡ ምርቶችንም በአገር ውስጥ ለመተካት በተደረገ ጥረት ውጤት መገኘቱን አብራርተዋል።
በቀጣይም የክልሉን ኢኮኖሚ ለማነቃቃት በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።
የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሊ መኮንን በበኩላቸው፤ በዞኑ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ለሚሰማሩ ባለሃብቶች የተጠናከረ ድጋፍ እንደሚደረግ ገልጸዋል።
"ነባር ባለሃብቶችን ከመደገፍ ባለፈ አዳዲስ ባለሃብቶችን በመሳብ ኢንቨስትመንቱን የማነቃቃት ስራ እየተከናወነ ነው" ያሉት ደግሞ የደቡብ ወሎ ዞን ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ሃላፊ ወይዘሮ ፋጡማ ይማም ናቸው።
ባለፉት ዘጠኝ ወራትም 14 ቢሊዮን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ 108 ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መሰጠቱን አስታውቀዋል።
ከመድረኩ ተሳታፊ ባለሀብቶች መካከል ሐጅ ኑሩ አህመድ፤ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ መንግስት የሰጠው ትኩረት በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮች እንዲፈቱ ማድረጉን ተናግረዋል።
በዚህም በቃሉ ወረዳ ሁለት ሄክታር መሬት ተቀብለው በ250 ሚሊዮን ብር ካፒታል በገነቡት ማምረቻ "አግማስ ውሃ" ማምረት መጀመራቸውን ገልጸዋል።
ሌላው ባለሃብት ሼህ ጀማል ሁሴን በበኩላቸው፤ ከ255 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ካፒታል በሐይቅ ከተማ ደሴ ዙሪያ ወረዳ ዱቄት እና ጠጠር ማምረቻ ፋብሪካዎችን እየገነቡ እንደሚገኙ አስታውቀዋል።
መሰረተ ልማትና ሌሎች ችግሮች መፈታታቸውን ጠቅሰው፤ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ወደ ማምረት ለመግባት እየሰሩ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
በመድረኩ የክልል፣ የዞን፣ የወረዳና የከተማ አስተዳደሮች አመራር አባላት፣ ባለሃብቶችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት የተገኙ ሲሆን፤ አግማስ ውሃ ፋብሪካም ተመርቆ በይፋ ስራ ጀምሯል።