በኦሮሚያ ክልል ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ የሚሰጡ ችግኞች ዝግጅት በስፋት እየተከናወነ መሆኑ ተገለጸ

620

አዳማ ፤ ሚያዚያ 7/2016(ኢዜአ)፡-  በኦሮሚያ ክልል በመጪው ክረምት የሚተከሉ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች ዝግጅት በስፋት እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

በክልሉ ግብርና ቢሮ የደን ልማትና እንክብካቤ ዘርፍ ዳይሬክተር አቶ ከተማ አብዲሳ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ በክልሉ ከጥር 1 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ለሁለት ወራት የአፈርና ውሃ እቀባ ስራ፣ የእርከን ማሰርና የተራቆቱ መሬቶችን ከንኪኪ ነፃ የማድረግ ስራ ተከናውኗል።

በዚህ ረገድ በምስራቅና ምዕራብ ሐረርጌ ዞኖች የተከናወነው የተፋሰስና እርከን ማሰር ስራ ለሌሎች የክልሉ ዞኖች ጭምር ተሞክሮ እንደሚሆን ተናግረዋል።

በአብዛኛው የተፋሰስ ልማት ስራ በተከናወነባቸው መሬቶች ላይ የሚተከሉ ችግኞችን በስፋት የማዘጋጀት ተግባርም ጎን ለጎን እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በክልሉ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ የሚሰጡ ችግኞችን የማዘጋጀት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸው የእስካሁኑ አፈጻጸምም የተሻለ መሆኑን አብራርተዋል።

የፍራፍሬ ችግኞች፣ ቀርከሃና ለጥምር ደን አገልግሎት የሚውሉ ችግኞች ትልቅ ትኩረት ማግኘታቸውን አመልክተዋል።

ከተዘጋጁት ችግኞች ውስጥ 40 በመቶ ለደን አገልግሎት የሚውልና 10 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ የፍራፍሬ ችግኞች መሆናቸውን የገለፁት አቶ ከተማ ፤ ለተከላ የበቁ ችግኞችን የመለየት ስራ እየተከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል።

የችግኝ መትከያ ጉድጓድ የማዘጋጀት ስራም እየተከናወነ ሲሆን በክልሉ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ ችግኝ ለመትከል መታቀዱንም ተናግረዋል።

በዚህም ከ800 ሺህ ሄክታር በላይ የሚሆነውን መሬት የመለየት ስራ መከናወኑን  ጠቅሰዋል።

የምስራቅ ሸዋ ዞን ግብርና ጽሕፈት ቤት ምክትል ሃላፊ አቶ አብነት ዘገየ በበኩላቸው ፤በዞኑ ዘንድሮ የሚተከል 279 ሚሊዮን የተለያየ አገልግሎት ያላቸው ችግኞች የማዘጋጀት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

በዞኑ 13 ወረዳዎች በተለዩ ከ300 በላይ ተፋሰሶች ላይ ለ60 ቀናት የአፈርና ውሃ እቀባ ስራ መከናወኑ አስታውሰው፤ በመጪው ክረምት የፍራፍሬ ጨምሮ ሌሎችንም ችግኞች ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

በተለይ ሀገር በቀል ዛፎች፣ የፍራፍሬ፣ ቀርከሃና ቴምርን ጨምሮ ለእንስሳት መኖ የሚውሉትን ለመትከል ከተፋሰስ ስራው ጎን ለጎን የጉድጓድ ዝግጁቱ አሁንም ተጠናክሮ መቀጠሉን አመልክተዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም