የብሔራዊ መታወቂያ ሥርዓት በቀጣይ ጊዜያት ለሚታሰቡ የልማት ውጥኖች መሠረት የሚጥል ነው

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 7/2016(ኢዜአ)፡- የብሔራዊ መታወቂያ ሥርዓት በቀጣይ ጊዜያት ለሚታሰቡ የልማት ውጥኖች መሠረት የሚጥል መሆኑን የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮጀክት ዋና ሥራ አስኪያጅ  ዮዳሄ ዘሚካኤል ገለጹ።  

የፋይዳ ቁጥር የዲጂታል መታወቂያ ሲሆን ቴክኖሎጂን በመጠቀም የነዋሪዎችን የተመጠነ የባዮሜትሪክና ዲሞግራፊክ መረጃ በመሰብሰብ “አንድ ሰው አንድ ነው” በሚል መርህ አንድን ሰው ልዩ በሆነ ሁኔታ መለየት የሚያስችል ሥርዓት ነው። 

በኢትዮጵያ የዲጂታል መታወቂያ ሥርዓት መዘርጋት ነዋሪዎች የመታወቂያ መብታቸው እንዲረጋገጥ ከመርዳት ባሻገር በአገር አቀፍ ደረጃም የግልጽነት፣ የተጠያቂነትና የተሳለጠ አሠራር ሥርዓትን ለመዘርጋት ያስችላል።   

የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያው ሕብረተሰቡ በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ተገቢውን አገልግሎት እንዲያገኝ ጉልህ እገዛ እንደሚያበረክትም ይገለጻል። 

የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮጀክት ዋና ሥራ አስኪያጅ ዮዳሄ ዘሚካኤል፤ የብሔራዊ መታወቂያ ሥርዓት ለዲጂታል ትራንስፎርሜሽን መሠረት የሚጥል መሆኑን ይናገራሉ።  

ብሔራዊ መታወቂያ የማንነት መገለጫ ሆኖ ማገልገል የሚችል ነው ያሉት ሥራ አስኪያጁ፤ ለዜጎች ቀልጣፋና ሕጋዊ አገልግሎት ተደራሽ እንዲሆን የሚያስችል ነው ብለዋል።  

አሁን ለማኅበረሰቡ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራዎች በሰፊው እየተሰሩ መሆናቸውን ገልጸው፤ ከትናንት ዛሬ የተሻለ ተቀባይነት በማግኘት ላይ መሆኑንም ገልፀዋል። 

ብሔራዊ መታወቂያን ቀላል በሆነ መንገድ ከፍቶ የፋይዳ ቁጥር ማግኘት እንደሚቻል የገለጹት ሥራ አስኪያጁ፤ በኢትዮጵያ በርካታ ሰዎች የነዋሪነት ማረጋገጫ አግኝተው ወደ ኢኮኖሚው እንዲቀላቀሉ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።  

በርካታ ሰዎችን ወደ ኢኮኖሚ ሥርዓቱ መቀላቀል መቻል የአገሪቱ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እድገት እንዲፋጠን የሚያስችል ነው ብለዋል። 

ዜጎች የፋይዳ ቁጥር በማግኘታቸው ወደ መደበኛ የኢኮኖሚው ሥርዓት እንዲቀላቀሉ፣ የንግድ ሥርዓቱ እንዲፋጠን እንዲሁም ከተለያዩ የፋይናንስ አማራጮች ብድርን ጨምሮ ተመሳሳይ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ የሚያስችል መሆኑንም ገልፀዋል። 

የብሔራዊ መታወቂያ ሥርዓት በቀጣይ ጊዜያት ለሚታሰቡ የልማት ውጥኖች መሠረት የሚጥል መሆኑንም ጠቁመዋል። 

ብሔራዊ መታወቂያ ሁሉንም ዜጎች የሚጠቅም ፕሮጀክት መሆኑን ጠቁመው፤ የተለያዩ የማጭበርበር ሥራዎችን የሚሰሩ እንዲሁም ከአንድ ማንነት በላይ ሆነው ተግባራትን ማከናወን የሚፈልጉትን የሚከላከል መሆኑንም ተናግረዋል። 

በሕጋዊ መንገድ የንግድ ሥራን ለማከናወን፣ የተቀላጠፈ አገልግሎት ለማግኘት፣ አዳዲስ ምርቶችን ለማስተዋወቅ፣ አገልግሎቶችን በዲጂታል መንገድ ለማቅረብና ለማግኘት እንዲሁም ሌሎች ተግባራትን ማከናወን ለሚሹ ዜጎች ጠቃሚ መሆኑንም ተናግረዋል። 

መታወቂያው ግልጽነት፣ ተጠያቂነት፣ አካታችና ፍትሃዊ የኃብት ክፍፍል እንዲኖር የሚያስችል መሆኑንም ገልፀዋል። 

እንደ ባንክ፣ ጤና፣ ኢንሹራንስና የመሳሰሉት ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ለኅብረተሰቡ የተፋጠነና ዘመናዊ አገልግሎት እንዲሰጡ ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥርም አቶ ዮዳሄ ተናግረዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም