ለኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ስኬታማነት የጃፓን መንግስት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል-በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ሺባታ ሂሮኖሪ

591

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 7/2016(ኢዜአ)፡- ለኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ስኬታማነት የጃፓን መንግስት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ሺባታ ሂሮኖሪ  ተናገሩ፡፡

የጃፓን መንግስት ከተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም (ዩኤንዲፒ) ጋር በመተባበር ለኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን 12 ተሸከርካሪዎችን በዛሬው ዕለት ድጋፍ አድርጓል።


 

በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ሺባታ ሂሮኖሪ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት የተሽከርካሪ ድጋፉን ለኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ አስረክበዋል።

በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ሺባታ ሂሮኖሪ በበኩላቸው የጃፓን መንግስት ከዚህ ቀደም ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የተለያዩ ድጋፎችን ማድረጉን ተናግረዋል፡፡

ይህ ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቅሰው፤ በዛሬው እለት የተከናወነው ድጋፍም የዚሁ ማሳያ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም (ዩኤንዲፒ) የኢትዮጵያ ተወካይ ሳሙኤል ዶው በበኩላቸው ችግሮችን ለመፍታት ብሎም ዘላቂ እድገትን ለማፋጠን ውይይት ቁልፍ ሚና እንዳለው የዓለም ተሞክሮ እንደሚያሳይ አውስተዋል፡፡


 

ከዚህ አኳያ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማስፈን ሀገራዊ ምክክሩ ሚናው የጎላ እንደሆነ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ፤ ኮሚሽኑ በሀገሪቱ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎችን አሳታፊ የሆነ ሀገራዊ ምክክር ለማካሄድ በርካታ ስራዎች እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።


 

ኮሚሽኑ አሁን ላይ በ10 ክልሎች እና በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የተሳታፊዎች ልየታ በማጠናቀቅ  ወደ ቀጣይ ምእራፍ ለመሸጋገር በሂደት  ላይ መሆኑን ጠቁመዋል።

ከዚህ አኳያ ድጋፉ  ኮሚሽኑ በተለያዩ አካባቢዎች በመንቀሳቀስ ለሚያከናውናቸው ስራዎች መቀላጠፍ ሚናው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የጃፓን መንግስት ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት እስካሁን ድረስ በአጠቃላይ 3 ሚሊዬን ዶላር  የሚጠጋ ድጋፍ ማበርከቱን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም