ለኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ዕጩ ጥቆማ መቀበል ተጀመረ

318

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 7/2016(ኢዜአ)፡- ኅብረተሰቡ ከዛሬ ጀምሮ ለኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የሴቶችና ሕፃናት ሰብዓዊ መብት ምክትል ኮሚሽነር እጩ መጠቆም እንደሚችል ተገለጸ።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የሴቶችና ሕፃናት ምክትል ኮሚሽነር ሥራ መልቀቃቸውን ተከትሎ የዕጩ አቅራቢ ኮሚቴ ተቋቁሞ ሥራ ጀምሯል።

ዕጩ አቅራቢ ኮሚቴው ስምንት አባላት ያሉት ሲሆን ከተለያዩ የሙያ ዘርፎች የተውጣጡና ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ መሆናቸው ተገልጿል።

የዕጩ አቅራቢ ኮሚቴውን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ በሰብሳቢነት ሲመሩት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ቴዎድሮስ ምህረት ምክትል ሰብሳቢ ናቸው።

የዕጩ አቅራቢ ኮሚቴው ጸኃፊ ባንቺይርጋ መለሰ በሰጡት መግለጫ፤ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የሴቶችና ሕፃናት ኮሚሽነር በፈቃዳቸው ሥራቸውን መልቀቃቸውን ተከትሎ ምትክ ለመሰየም የምልመላ መሥፈርትና የውስጥ አሠራር መመሪያ ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ ተገብቷል።

በዚህም ኅብረተሰቡ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ሚያዚያ 22/2016 ዓ.ም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሚገኘው የዕጩ አቅራቢ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት በአካል በመቅረብ፣ በኢሜል፣ በፖስታና በኦንላይን ጥቆማ መስጠት እንደሚችል ገልጸዋል።

ለኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የሴቶችና ሕጻናት ምክትል ኮሚሽነርነት የሚመረጡት ሴት እጩ ተወዳዳሪ ማሟላት ያለባቸው መሥፈርቶችንም አብራርተዋል።

ከመሥፈርቶቹ መካከልም ለሰብዓዊ መብቶች መከበር ተቆርቋሪ የሆኑ፣ በሕግ ወይም አግባብነት ባለው ሙያ ሰፊ ልምድና ዕውቀት ያላቸው፣ በሥነ-ምግባርና በሥራ ታታሪነት የተመሰገኑ እንዲሁም የየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ አባል ያልሆኑ የሚሉት ይገኙበታል።

ኮሚቴው ከጥቆማ በኋላ ዕጩዎችን በመሥፈርቱ መሰረት የመለየትና የማጣራት ሥራ በመሥራት በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ለምክር ቤቱ የሚያቀርብ መሆኑንም ነው ጸኃፊዋ ያመለከቱት።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 55/14/ አዋጅ መሠረት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንን የማቋቋም ተቋሙን የሚመሩ አባላትን የመሰየምና ሥልጣንና ተግባራቸውን በሕግ የመወሰን ሥልጣን አለው።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተጠሪ ከሆኑ የዴሞክራሲ ተቋማት መካከል አንዱ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም