የሕዝብ በዓላትና የበዓላት አከባበር ረቂቅ አዋጅ ለሕዝብ አብሮነት እና መተሳሰብ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ተጠቆመ

246

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 7/2016(ኢዜአ)፡-የሕዝብ በዓላትና የበዓላት አከባበር ረቂቅ አዋጅ ለሕዝብ አብሮነት እና መተሳሰብ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ተጠቁሟል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ማሕበራዊ ልማት፣ ባሕልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እና የሕግ እና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ረቂቅ አዋጁን በተመለከተ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አድርጓል።

ረቂቅ አዋጁ የኢትዮጵያን መብት እና ጥቅም ያስከበረ፣ ትውልድ ተሻጋሪ፣ ግጭትና ንትርክን እንዲያስቀር ታስቦ እንደሚወጣ የጤና፣ ማሕበራዊ ልማት፣ ባሕልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ወርቅሰሙ ማሞ ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም ረቂቅ አዋጁ፣ ዘመኑን የዋጄ፣ ህጋዊ ዕውቅና ኖሮት ለሕዘብ አብሮነት እና መተሳሰብ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ሰብሳቢዋ አብራርተዋል፡፡

የሕግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ እጸገነት መንግስቱ በበኩላቸው በረቂቅ አዋጁ ዙሪያ መስተካከል ያለባቸው ጉዳዮቸ ካሉ እንደሚስተካከሉ ጠቅሰው፣ በውይይቱ ጠቃሚ ግብዓት መገኘቱን ተናግረዋል፡፡


 

የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው፣ የካቲት 12 በርካታ ኢትዮጵያዊያን የተጨፈጨፉበት ዕለት ሆኖ ሳለ በረቂቅ አዋጁ ታስቦ ይውላል ከሚባል ተከብሮ እንዲውል ቢደረግ የሚል አስተያየት ሰንዝረዋል፡፡ 

እንዲሁም፣ ሃይማኖታዊ እና ብሔራዊ በዓላት በሚከበሩበት እለት በአልባሳት እና በቦታ ምክንያት ከጸጥታ አስከባሪዎች ጋር ከፍተኛ አለመግባባት ሲፈጠር ይስተዋላልና ችግሩን ለመፍታት ምን ታስቧል? የሚል ጥያቄም ተነስቷል፡፡


 

የባሕልና ስፖርት ሚኒስትር አቶ ቀጄላ መርዳሳ በበኩላቸው ምንም እንኳ አሰቃቂ ጭፍጨፋ ቢደርስም፣ የየካቲት 12 በአል ቀደም ሲልም ታስቦ እንጂ ተከብሮ ስለማያውቅ እለቱ ታስቦ እንደሚውል መግለጻቸውን ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተገኘመው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም