ጄኔራል አበባው ታደሰ አሁናዊ የሠላም ሁኔታን በተመለከተ ከማዕከላዊ ሸዋ ኮማንድ ፖስት ጋር ተወያዩ

361

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 7/2016(ኢዜአ)፦ የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል አበባው ታደሰ በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ እና የሰሜን ሸዋ ዞን አሁናዊ የሰላምና ፀጥታ ሁኔታ እንዲሁም በወደፊት የሥራ አቅጣጫ ላይ ከማዕከላዊ ሸዋ ኮማንድ ፖስት ጋር ተወያይተዋል፡፡ 

ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ የማዕከላዊ ሸዋ ኮማንድ ፖስት አሸባሪውን ሸኔ እና ራሱን ፋኖ ብሎ የሚጠራውን ፅንፈኛ ኃይል አከርካሪውን በመስበር በሁለቱም ዞን አንፃራዊ ሰላም መስፈን መቻሉን አረጋግጠዋል፡፡ 

ጄኔራል አበባው ታደሰ በከሚሴ ከተማ ከማዕከላዊ ሸዋ ኮማንድ ፖስት ከፍተኛ አመራሮችና ከሁለቱም ዞን ከተውጣጡ የአስተዳደር አካላት ጋር ባደረጉት ውይይት ፅንፈኛው ኃይል አዲስ አበባን ለማተራመስ ይመቸኛል ብሎ አለኝ ያለውን ኃይል በሰሜን ሸዋ ዞን ውስጥ ሰግስጎ እንደነበረ አስታውሰዋል። 


 

የማዕከላዊ ሸዋ ኮማንድ ፖስት በወሰደው ፈጣን እርምጃ በሁለቱም ዞን የነበሩ ሁለት ቋንቋ ተናጋሪ ፅንፈኞችን በመደቆስ ሀገር የማተራመስ ቀቢፀ ተስፋቸውን በማምከን ምርጥ ውጤት ማስመዝገቡን ገልፀዋል። 

አሁን ለብቻው ተነጥሎ በየሸጡ ተደብቆ የሚገኘውን የፅንፈኛ ኃይል አመራሮችን የመመንጠሩ ስራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ጄኔራል መኮንኑ አሳስበዋል፡፡ 

የማዕከላዊ ሸዋ ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢና የኮማንዶና አየር ወለድ አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ሹማ አብደታ በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔራሰብ እና ሰሜን ሸዋ ዞን የሀገሪቷን ሰላም በማናጋት የህዝቦቿን በሰላም የመኖር ዋስትናን ለማሳጣት ቆርጠው የተነሱትን ሁለቱንም ፅንፈኛ ኃይሎች በተገቢው መንገድ በመምታት የጥፋት ተልዕኳቸውን ማኮላሸት መቻሉን ገልፀዋል። 


 

ኮማንድ ፖስቱ ከኦፕሬሽናል ስራው ጎን ለጎን የአካባቢውን የፀጥታ ኃይል የማጠናከርና የማደራጀት ስራዎችን መስራቱን በማስታወስ አሁን በሁለቱም ዞን ለፀጥታው ኃይል ተግዳሮት የሚሆን ሃይል እንደሌለም አረጋግጠዋል፡፡ 

የውይይቱ ተሳታፊውችም የሀገር መከላከያ ሠራዊታችን ራሱ ሞቶ ዜጎችን የሚያኖር ህዝባዊ ሀይል መሆኑን በማስታወስና በዞናቸው ለተገኘው ሰላም ሠራዊቱ ለከፈለው መስዋዕትነት እና ላስመዘገበው ከፍተኛ ውጤት የላቀ ክብር እንዳላቸው አብራርተዋል። 

አሁን የፅንፈኞችን ሴራ ህዝባችንም በተገቢው መንገድ ስለተገነዘበ እኛም ሆነ ህዝባችን ከሠራዊታችን ጎን ስለሆን የዚህን ሀይል ርዝራዦች ለማጥፋት ብዙም አስቸጋሪ እንደማይሆን እምነታቸውን ገልፀዋል፡፡ 

በመጨረሻም በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረስብ ዞን በዞኑ ለስመዘገቡት የተራጋጋ ሰላምና ፀጥታ እውቅና በመስጠት ለሠራዊቱ አመራሮች ልዩ ሽልማት ከምስጋና ጋር ማበርከታቸውን የመከላከያ ሠራዊት መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም