ቀጥታ፡

ለኢትዮጵያ የመረጃና ደኅንነት ዘርፍ እድገት  ጉልህ ሚና ያበረከቱት ዶ/ር አምባሳደር አስማማው  ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ

 አዲስ  አበባ ፤ መጋቢት 6/2016  (ኢዜአ) ፦ ለኢትዮጵያ የመረጃና ደኅንነት ዘርፍ እድገት ውስጥ ጉልህ ሚና ያበረከቱት ዶ/ር አምባሳደር አስማማው ቀለሙ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።

 የብሔራዊ መረጃና ደኀንነት አገልግሎት   ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከው  መግለጫ እንዳለው   ከ1956 ዓ.ም ጀምሮ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም እና ደኅንነት በማስጠበቅ ለ60 ዓመታት ያህል በመረጃና ደኅንነት ዘርፍ ሰፊ አበርክቶት ሲያደርጉ የቆዩት ዶ/ር አምባሳደር አስማማው ቀለሙ በተወለዱ በ84 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።

ዶ/ር አስማማው ቀለሙ በሀገር ዉስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ከማገልገል በተጨማሪ የሀገር ዉስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትር በመሆን አገልግለዋል።

ዶ/ር አስማማው ቀለሙ በኢኮኖሚክስ የትምህርት ዘርፍ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ከእስራኤል ሀገር፣ የሦስተኛ ዲግሪያቸውን ከቡልጋሪያ ካርል ማርክስ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ኢኮኖሚክስ እንዲሁም ፖስት ዶክትሬታቸውን እንግሊዝ ሀገር ከሚገኘው ለንደን ስኩል ኦፍ ኢኮኖሚክስ አግኝተዋል።

ከእነዚህም በተጨማሪ በፖሊስነት ህይወታቸው የ9ኛ ኮርስ አባል የነበሩ ሲሆን በዘርፉ የኮለኔልነት ማዕረግ ላይ ደርሰዋል።

ዶ/ር አስማማው ቀለሙ በድህረ የኢትዮ- ሶማሊያ ጦርነት በሶማሊያ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር በመሆን በሁለቱ ሀገራት መካከል ሠላም እንዲሰፍን እና የእስረኞች ልውውጥ እንዲደረግ የአንበሳውን ድርሻ ተጫውተዋል።

ዶ/ር አስማማው ቀለሙ በቀጠናው የኢትዮጵያን ጂኦ-ስትራቴጂካዊ ጥቅም ለማስጠበቅ እልህ አስጨራሽ ትግል በማድረግ የሚታወቁ ታላቅ የመረጃና ደኅንነት ባለሙያ ነበሩ።

የመረጃና ደኅንነት ሙያን በተመለከተ በእስራኤል እና በጀርመን የተለያዩ ሥልጠናዎችን በመከታተል እና ሙያዊ እውቀትን፣ ክህሎትን፣ አስተሳሰብን እና ሰብዕናን መሰረት አድርጎ አሻጋሪ ተቋም በሀገር ውስጥ እንዲገነባ በ1974 ዓ.ም የስትራቴጂክ ጥናት ኢንስቲትዩትን በማቋቋም ከፍተኛ አስተዋጾ አድርገዋል።

በአጼ ኃይለ ሥላሴ እና በደርግ ዘመነ መንግስት የኢትዮጵያን ጥቅም እና ደኅንነት ለማስጠበቅ ከፍተኛ ስራ የሰሩት ዶ/ር አስማማው ቀለሙ በኢህአዴግ ዘመነ መንግሥት ምንም ክስ ሳይቀርብባቸው ለ12 ዓመታት በእስር ቤት እንዲያሳልፉ የተደርጉ ሲሆን በእስር በቆዩባቸው ዓመታትም ሳይቀር ታራሚዎች የትምህርት እድል እንዲያገኙ እና ትምህርት እንዲስፋፋ በማድረግ ሀገራዊ ኃላፊነታቸውን ተወጥተዋል።

ከእስር ከወጡ በኋላም ዘመን ባንክን ጨምሮ በተለያዩ የግል ተቋማት በአማካሪነት እና ኃላፊነት አገልግለዋል።

ዶ/ር አስማማው ቀለሙ ከ2010 ዓ.ም ሀገራዊ ለውጥ በኃላ በተደረገላቸው ተቋማዊ ጥሪ መሰረት የጤና መታወክ እስካጋጠማቸው ታህሳስ 2016 ዓ.ም ድረስ በብሔራዊ ደኅንነት ዩኒቨርሲቲ በማስተማር ላይ የነበሩ ሲሆን በተለያዩ ሚዲያዎች በመቅረብ በተለያዩ ወቅታዊ ሀገራዊ፣ ቀጠናዊ እና ዓለም አቀፋዊ የደኅንነት፣ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ በሳል ትንታኔ በመስጠት ሀገራዊ ኃላፊነታቸዉን በታማኝነት እና በቅንነት ተወጥተዋል።

ዶ/ር አስማማው ቀለሙ የሀገር ብሔራዊ ጥቅም እና ደኅንነት የማስጠበቅ ስራ ከወገንተኝነት የጸዳ፣ የእድሜ ልክ እና በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ቅድሚያ የሚሰጠው ሥራ መሆኑን በተግባር ያሳዩ ባለሙያ ነበሩ።

ዶ/ር አስማማዉ ቀለሙ ባደረባቸዉ ህመም በሀገር ዉስጥ እና በዉጭ ህክምና ሲደረግላቸው ቢቆዩም ቅዳሜ ሚያዝያ 05/ 2016 ዓ.ም ሌሊት ላይ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።

ዶ/ር አስማማው ቀለሙ ባለትዳር እና የሦስት ወንድ ልጆች አባት ነበሩ።

የዶ/ር አስማማው ቀለሙ የቀብር ሥነ-ሥርዓት ማክሰኞ 9 ሰዓት ወዳጅ ዘመዶቻቸዉ እና የስራ ባልደረቦቻቸዉ በተገኙበት በቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን የሚፈፀም ይሆናል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም