የታላቁ ህዳሴ ግድብ ''እራትም... መብራትም'' የመሆን ጅማሬ

1577

ሲሳይ ማሞ (ከአሶሳ)

ያኔ! 2003 ዓ.ም የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ ሲቀመጥ የተነገሩ ተስፋዎች የማየፈቱ ህልሞች ብለን ስንቶቻችን አስበናቸው ይሆን? በአካባቢው ሊኖር ስለሚችለው ታላላቅ ክስተቶች፣ ስለሚፈጠሩት መልካም ነገሮች በሰማንበት ቅጽበት በህልም ዓለም ውስጥ እንዳለን ስንቶቻችን አስበን ይሆን? "አዬ ህልም!?" በሚል ሲደርስ እናየዋለን በሚል ቀናት ቆጥረናል። ያኔ! ነገሮች ሲነሱና ሲተረኩ ስንቶቻችን እንሆን እዚህ ቀን ላይ ደርሰን እናይ ይሆን!? የሚል ሃሳብ በእዝነ ህሊናችን የተመላለሰው? 

ያኔ! የታላቁ ህዳሴ ግድቡ ሲጠናቀቅ ወደ ኋላ ከ240 በላይ ኪሎ ሜትሮችን የሸፈነ ውሃ ሐይቅ ሰርቶ ተንጣሎ እንደሚተኛ እያለምን መጩውን ዘመን በጉጉት የጠበቅን ስንቶቻችን ነን? ግድቡ ግንባታው ሲገባደድ አገር የኤሌክትሪክ ኃይል ከማመንጨት በዘለለ "ከሰው ሰራሽ ሐይቁ በሚወጣ ዓሳ ሌላ የገቢ ምንጭ ይፈጠርላታል፤ በሚፈጠረው ሰው ሰራሽ ሃይቅ ላይ የጀልባ ትራንስፖርትና የመዋኛ አገልግሎቶች ይጀመራል" የሚሉት መረጃዎችንና ትንታኔዎችን ከመገናኛ ብዙሃኑ ስንሰማ እንደርስ ይሆን? የሚል ጥያቄ ወደ አእምሯቸው ያልመጣ ቢኖሩ ጥቂቶች ሳይሆኑ አየቀሩም።

ያኔ! እንደትንቢት የተነገረው ዛሬ ጊዜው ሲደርስ "ይሆናል" የተባለው ከጊዜ ወደ ጊዜ "እየሆነ" መጣ። ስለታላቁ ግድብ በህልም ደረጃ ሲገለፁ የነበሩ በዕውን ወደማሳየቱ እየተንደረደረ ይገኛል። ከዚሁ ጉዳይ ጋር የተያያዘ ገጠመኜን ጀባ ልበላችሁ!

ዕለቱ መጋቢት 23 ቀን 2016 ዓ.ም. ከማለዳው 12 ሰዓት ነው፡፡ አፍንጫዋ ላይ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ የሰካች አንድ የሞተር ጀልባ ከደቡብ ወደ ሰሜን የተንጣለለውን ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ሰው ሰራሽ ሐይቅ ለሁለት እየከፈለች ትጓዛለች ከማለት ትበራለች ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ሰው ሰራሽ ሐይቁ ውሃውን እንደልቧ እየቀዘፈች ለመጓዝ አስችሏታልና!

ከምዕራብ በኩል የኮርቻ ግድብ (Saddle dam) ተጠማዞ እና በኩራት ደረቱን ገልብጦ ይታያል፡፡

በስተምስራቅ አቅጣጫ ላይ የሚገኘው የግድቡ ሃይቅ ደግሞ ለስለስ ያለ ሃምራዊ ቀለም ለተመላካቹ ያሳያል። የማለዳዋ የፀሐይ ጨረር ያረፈበት የውሃው ክፍል ለእይታ ባያስቸግርም ገና ከማለዳው ከአካባቢው ሞቃታማ አየር ጋር ተዳምሮ ወላፈን የሚመስል ሙቀቱን መርጨት ጀምሯል፡፡ ከፊት ለፊታችን ደግሞ በረጅም ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ያቆረው ሰው ሰራሽ ሐይቅ ፊት ለፊት ተንጣሎ ይታያል፡፡ 

የተሳፈርንባት የሞተር ጀልባ ስምንት ያህል መንገደኞችን ይዛለች፡፡ በሰው ሰራሽ ሐይቁ ላይ የሚደረግ ጉዞ ለተጓዡ ሐሴትን ጀልባዋን ለሚዘውራት ከዕለት ገቢ የዘለለ ተድላን እንደሚለግስ አያጠራጥርም። የአካባቢውን ድባብ እየተመለከትን ጉዟችንን ቀጠልን። በጉዞው ቅፅበትም ዓይኖቻችን በአንድ ወጣት አሳ አስጋሪ ላይ አረፉ።

ወጣቱ በጀልባዋ ላይ ሆኖ በአንደኛው አቅጣጫ በኩል አጎንብሶ በመንጠቆ ያጠመዳቸውን ግዙፍ አሳዎችን አጥብቆ እየያዘ ወደ ጀልባዋ ይጨምራል። ከአቅሙ በላይ ሆነው ሊያመልጡት የሚታገሉ አሳዎችን ደግሞ በብረት አንካሴ ወገባቸውን እየወጋ ለመያዝ ይታገላል፡፡ ተጠግተን ለመርዳትና አሳዎቹን በመያዝ ለማገዝም ሆነ ሌላ ድጋፍ ለማድረግ አልደፈርንም፡፡ ወጣቱ ግዙፍ አሳዎቹ ጋር የገጠመውን ግብግብ በካሜራ ለማስቀረት ጥረት ማድረጉን ግን አልዘነጋሁትም።

ወጣቱ ኢትማን መሃመድ ይባላል። በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን የጉባ ወረዳ ነዋሪ ነው፡፡ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ሐይቅ ላይ አሳ የማስገር ስራ ከጀመረ ወራት አስቆጥሯል፡፡

“ቤተሰቦቼ እንደነገሩኝ ከ13 ዓመት በፊት ግድቡን ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ ሲቀመጥ አሁን በሞተር ጀልባ የምንጓዝበት ሃይቅ ይፈጠራል የሚል እምነት በአካባቢው ነዋሪዎች እሳቤ ውስጥ ፈጽሞ አልነበረም።” ሲል ይናገራል ወጣቱ፡፡ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሃይቅ ለእርሱ እና ለሌሎች ከእርሱ ጋር ለተደራጁ 25 ወጣቶች የሥራ እድል በር መክፈቱን አጫወተኝ፡፡ ከታላቁ ግድብ ያገኙት ትሩፋት እርሱ እና የማህበሩ አባላት በአገራቸው ላይ ሰርተው የመለወጥ ተስፋቸውን በእጅጉ እንዳለመለመላቸው አጫውቶኛል፡፡

ከዚህ ቀደም በአካባቢው ከሚገኙ ወንዞች አሳ ቢያመርቱም በህዳሴው ግድብ አማካኝነት ከተፈጠረው ሰው ሰራሽ ሐይቅ የሚያገኙት ግን በዓይነትም በመጠንም የተለየ እንደሆነ ይናገራል። ከሐይቁ እስከ 50 ኪሎ ግራም የሚመዝኑ ነጫጭና ሌሎች ዓሳዎችን እያሰገረ መሆኑን በአድናቆት ጭምር ይገልፃል። ማህበሩ በቀን እስከ ሁለት ኩንታል ወይም ሁለት መቶ ኪሎ ግራም ገደማ  ዓሳ ያመርታል፡፡ 

“የህዳሴው ግድብ የምግብ ዋስትናም ፤ የገቢ ምንጭም ሆኖናል” ሲልም ወጣቱ ሃሳቡን ቋጭቷል።

ለሰዓታት በቆየሁበት የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሰው ሰራሽ ሐይቅ የአሳ ማስገር እንቅስቃሴ ላይ ኢትዮጵያውያን በአንድነት መንፈስ ከገነቡት ግድብ የስራ ዕድል ተጠቃሚ የመሆን ጅማሬን ይስተዋላል። ነገሩ እንዲህ ነው! በባህር ዳር ጣና ሃይቅ ላይ ያካበተውን የአሳ መረብ አሰራር እና የሞተር ጀልባ አጠቃቀም ልምድ ለማካፈል ወደ ስፍራው ያቀናው ወጣት የሻምበል ወርቁ በማህበር ተደራጅተው አሳ ለሚያሰግሩት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ወጣቶች ስልጠና ሲሰጥ ማግኘቴ ቀደም ብዬ የጠቀስኩትን መረጃ እውነታነት ያሳያል።

“አንዱ ወንድሜ ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ ይሄም ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እኔም ከአማራ ክልል ነኝ፡፡ ሁላችንም እኩል የግድቡ ትሩፋት ተጠቃሚ ነን፡፡ ከዚህ ቀደም በአካል የማንተዋወቀውን ኢትዮጵያውያንን ግድቡ አስተዋውቆናል” ብሎኛል የሻምበል።

ሌላው የመንጠቆ አጣጣል ስልጠና ለመስጠት ከአርባምንጭ ተጉዞ ወደ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ሰው ሰራሽ ሐይቅ መጥቶ ያገኘሁት ደግሞ ወጣት አልማው ደሳለኝ ነው።

''ለአካባቢው ወጣቶች ልምዴን እና ያለኝን ዕውቀት በማካፈሌ በእጅጉ ደስተኛ ነኝ'' የሚለው ወጣቱ፤ በሃይቁ ላይ የተመለከተው ከፍተኛ የአሳ ሃብት እንደ እርሱ ያሉ ሌሎች ኢትዮጵያውያንን በመጥቀም ለአገሪቷም የተሻለ ገቢን ሊያመጣ እንደሚችል ያምናል። 

“ተባብረን በመስራት አገራችንን እንለውጣለን” በማለት ህብረትና አንድነት ከድህነት ለመውጣት የሚያስችል ዘመኑ የሚፈልገው ታላቅ መሳሪያ መሆኑን ያምናል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ተገንብቶ ሲጠናቀቅ ...ተብለው ሲነገሩ የነበሩ የወደፊት ትልሞች አሁን እውን ሆነው 'ስራን ለሰሪው....ፍፁማዊ የገፅታ ለውጥን ለአካባቢው መልክዓ ምድር እንዲሁም ሰፊ የቱሪዝምና ሌሎች የስራ መስኮችን ለሚመለከተው አካል ለመስጠት የተግባር ጅማሬ እየታየ ነው። በግድብ ግንባታው የመሰረት ድንጋይ ማኖር ወቅት "በይሆናል" ሲባሉ የነበሩ ዕቅዶች እውን ወደ መሆን...ወደ መጨበጥ እየመጡ መሆናቸው ይበል የሚያሰኝ ተግባር ነው።

ለኢትዮጵያውያን የ”ይቻላል” ተምሳሌት የሆነው ግድብ ዋነኛ በይበልጥ ሲጠቀስ ከነበረው የኃይል አቅርቦት ባሻገር ለዜጎች ሌላ የስራ መስክ በመፍጠር ' እራትም መብራትም' ሆኖ እስከመጨረሻው ሊዘልቅ እነሆ ውጤቱን እያሳየ ነው። እንግዲህ የነገ ሰው ብሎን ትሩፋቱን በይበልጥ ያሳየን !!

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም