26ኛው መላው የኦሮሚያ የስፖርት ውድድር በጅማ ከተማ መካሄድ ጀመረ

1021

ጅማ፣ ሚያዚያ 6/2016(ኢዜአ)፦  በኦሮሚያ የተለያዩ ዞኖችና ከተማ አስተዳደሮች የሚሳተፉበት 26ኛው መላው የኦሮሚያ የስፖርት ውድድር ዛሬ በጅማ ከተማ መካሄድ ጀመረ።

ውድድሩ በ21 ዘመናዊ የስፖርት አይነቶች የሚካሄድ ሲሆን በክልሉ የሚገኙ የተለያዩ ዞኖች እና ከተማ አስተዳደሮች እንደሚሳተፉበት ታውቋል።

በውድድሩ መክፈቻ መርሃግብር ላይ የተገኙት የኦሮሚያ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ሀላፊ  አቶ ማቴዎስ ሰቦቃ እንዳሉት ስፖርት ወዳጅነትና አንድነትን ያጎለብታል።


 

ስፖርት ዘርፈ ብዙ ማህበራዊ ጠቀሜታ እንዳለው ጠቅሰው ዛሬ በጅማ ከተማ የተጀመረው ውድድር ለ15 ቀናት እንደሚቆይ ገልጸዋል።

ስፖርት አብሮነትን ከማጠናከር ባለፈ ለአካልና ለአዕምሮ ብቃት ወሳኝ ነው ያሉት ሃላፊው፣ በክልሉ ብቁ ታዳጊ ስፖርተኞችን ለማፍራት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ኦሮሚያ የአትሌቶች መፍለቂያ መሆኗን አስታውሰው፣ ከክልሉ ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚያስጠሩ ስፖርተኞችን የማፍራት ስራው ይጠናከራል ብለዋል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጂራ በበኩላቸው  ታዳጊ ሕጻናት እና ወጣቶችን በዚህ መሰል የስፖርት መድረክ ማሳተፍ የሚበረታታ ነው ብለዋል።


 

ሀገራችን በተለያዩ የስፖርት አይነቶች ብቁና ተወዳዳሪ ወጣት ስፖርተኞችን ማፍራት እንድትችል በየአካባቢው ወጣቶችን ያሳተፈ ሥራ መስራት ያስፈልጋል ሲሉ ገልጸዋል ።

ይህም ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን የስፖርት ተሳትፎ ለማሳደግ ያግዛል ያሉት አቶ ኢሳያስ፣ በየደረጃው ለታዳጊ ወጣቶች ትኩረት መስጠት እንደሚገባ አሳስበዋል።

የጅማ ከተማ ከንቲባ አቶ ጣሃ ቀመር በበኩላቸው የጅማ ከተማና የጅማ ዞን ህዝብ ለውድድሩ የመጡ እንግዶችን በእንግዳ አክባሪነት ተቀብሎ እንዲያስተናግድ አስገንዝበዋል።  


 

ስፖርት በባህሪው አዝናኝና አንድነትን የሚያጠናክር መሆኑን ገልጸው፣ እንግዶች በጅማ ቆይታቸው የከተማዋን የተለያዩ አካባቢዎች እንዲጎበኙ ጠይቀዋል።

ዛሬ በጅማ ከተማ በተጀመረው የመላው ኦሮሚያ ስፖርት ውድድር 21 ዞኖች እና 23 የከተማ አስተዳደሮች እንደሚሳተፉ ለማወቅ ተችሏል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም