የትምህርት ለትውልድ መርሃ-ግብር በተግባር የታገዘ መማር ማስተማር ተደራሽ ለማድረግ ትልቅ እገዛ አድርጓል - ኢዜአ አማርኛ
የትምህርት ለትውልድ መርሃ-ግብር በተግባር የታገዘ መማር ማስተማር ተደራሽ ለማድረግ ትልቅ እገዛ አድርጓል
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 6/2016(ኢዜአ)፦ የትምህርት ለትውልድ መርሃ-ግብር በተግባር የታገዘ የመማር ማስተማር ተደራሽ ለማድረግ ትልቅ እገዛ ማድረጉን ኢዜአ ያነጋገራቸው ርዕሳነ መምህራን፣ መምህራንና ተማሪዎች ገለጹ፡፡
የትምህርት ለትውልድ የትምህርት ቤቶች ደረጃ ማሻሻያ መርሃ ግብር ሰኔ 2015 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር) አማካኝነት መጀመሩ ይታወሳል፡፡
መርሃ ግብሩም በዋናነት ማህበረሰብን በማሳተፍ በሀገር አቀፍ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ለመማር ማስተማር ምቹ ማድረግ ላይ የሚሰራ ነው።
በመርሃ ግብሩ እድሳት ከተከናወነላቸው ትምህርት ቤቶች መካከል በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኘው የደጃች ባልቻ አባሳፎ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አንዱ ነው፡፡
የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር ገዛኸኝ አጀመ የትምህርት ለትውልድ መርሃ ግብር በትምህርት ቤታቸው የተሻለ የቤተ-ሙከራና ቤተ መፅሃፍት ክፍል እንዲኖር ማድረጉን ጠቁመዋል።
ይህም በተግባር የታገዘ የመማር ማስተማር ምህዳር መፍጠሩን ጠቅሰዋል፡፡
በትምህርት ቤቱ የታሪክ መምህር የሆኑት ከፍያለው እንዳለው የትምህርት ለትውልድ መርሃ ግብር የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ የሚያስችሉ ግብዓቶች እንዲሟሉ ማድረጉን ጠቁመዋል፡፡
በተለይ ከንድፈ ሃሳብ ባሻገር በተግባር የተገዘ ትምህርት ለመስጠት ከፍተኛ ሚና ማበርከቱን ነው የጠቆሙት፡፡
ከትምህርት ቤቱ ተማሪዎች መካከል ሀና ዘውዱና ኤልሮኢ ተስፋዬ መርሃ ግብሩ የንድፈ ሃሳብ ትምህርትን በተግባር የተደገፈ በማድረግ የተሻለ እውቀት እዲያገኙ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡
የፍሬህይወት አንደኛና መካከለኛ ትምህርት ቤት መምህር ቁምላቸው ባዩ በበኩላቸው በመርሃ ግብሩ ብቁ ሀገር ተረካቢ ትውልድ ለመገንባት መሰረት የሚጥሉ ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል፡፡
በትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት ፕሮግራሞችና ጥራት ማሻሻል መሪ ሥራ አስፈፃሚ ዮሃንስ ወጋሶ፤ በመርሃ ግብሩ ስኬታማ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በመርሃ ግብሩ እስካሁን ባለው ሂደት በሀገር አቀፍ ደረጃ ካሉት 56 ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ግማሽ ያህሉ 27 ሺህ ትምህርት ቤቶች ከቀላል ጥገና እስከ ከፍተኛ እድሳት እንደተደረገላቸው አስታውቀዋል።
በተጨማሪም 4 ሺህ 800 አዳዲስ ቅድመ መደበኛ፣ 1ኛ እና 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ግንባታ ስራ ተጠናቆ አገልግሎት እንዲሰጡ መደረጉን አስረድተዋል።
ማህበረሰቡ በገንዘብ፣ ቁሳቁስና ጉልበት በአጠቃላይ 25 ቢሊዮን ብር የሚገመት ድጋፍ ማድረጉንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡