ምቹ የመኖሪያና የሥራ አካባቢ በመፍጠር ሁሉን አቀፍ ልማት ለማሳካት የተቀናጀ ርብርብ ሊደረግ እንደሚገባ ተመላከተ

864

ድሬዳዋ፤ ሚያዝያ 5/2016(ኢዜአ)፦ ለዜጎች ምቹ የመኖሪያና የሥራ አካባቢ በመፍጠር የተጀመረውን ሁሉን አቀፍ ልማት ለማሳካት የተቀናጀ ርብርብ እንዲደረግ የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን አስገነዘበ።

በድሬዳዋ ከተማ "የፕላስቲክ አጠቃቀም ዘይቢያችንን እናዘምን" በሚል መሪ ሃሳብ የንቅናቄ መድረክ ዛሬ በይፋ ተጀምሯል።

በመድረኩ "ብክለት ይብቃ፤ ውበት ይንቃ" በሚል መሪ ሃሳብ የተዘጋጀ ሲሆን፤ በድሬዳዋ አስተዳደር ደረጃ የሚካሄደው የአካባቢ ብክለት የመከላከል ንቅናቄ አካል ነው።

የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ፍሬነሽ መኩሪያ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት ንቅናቄው አካባቢን እየጎዳ ያለውን የፕላስቲክ ቆሻሻ ብክለትን ለመቀነስ ያለመ ነው።

የፕላስቲክ ብክለት በሰውና በእንሰሳት ጤና ላይ ከፍተኛ ችግር እያደረሰ መሆኑንም ገልጸዋል።

ከአነስተኛ እስከ ዋና ዋና ከተሞቻችን በፕላስቲክ ቆሻሻ የተጥለቀለቁ፣ የኑሮና የስራ ሂደቶችን እያደናቀፉ ለብዝሃ ህይወት መመናመን ምክንያት እየሆኑ ይገኛሉ ብለዋል።

በመሆኑም ይህንን በማህበራዊና የምጣኔ ሃብት እንቅስቃሴዎች ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ የሚፈጥረውን ችግር በተቀናጀ ህዝባዊ ንቅናቄ በመታገዝ መፍትሄ ለማምጣት ርብርብ እንዲደረግ አሳስበዋል።

በተለይም ችግሩን ለመቀነስ የተዘጋጁ ስትራቴጂ፣ የህግ ማዕቀፎችና የማስፈፀሚያ ስልቶችን በተቀናጀ መንገድ በመተግበር ዘላቂ የአካባቢ አጠቃቀም ለመፍጠር መሥራት እንደሚያስፈልግም አብራርተዋል።

በተጨማሪም በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚደርሰውን የደን መራቆትና የተፈጥሮ ሃብት መመናመን ችግር ለመታደግ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን መተግበር ይገባል ብለዋል።

ባለሥልጣኑ በአስተዳደሩ ለተጀመረው ህዝባዊ ንቅናቄ ስኬት ድጋፍ እንደሚያደርግም ወይዘሮ ፍሬነሽ አረጋግጠዋል።


 

የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ሀርቢ ቡህ በበኩላቸው በንቅናቄው የአካባቢ ፖሊሲና የህግ ማዕቀፎች በተቀናጀ መንገድ በመተግበር ምቹ የሥራ፣ የመኖሪያ እና የኢንቨስትመንት መዳረሻ ከተማ ለመፍጠር እንደሚሰራ ተናግረዋል።

የተጀመረው ንቅናቄ በሚቀጥሉት ስድስት ወራት በአስተዳደሩ በፕላስቲክ፣ በአየር፣ በውሃ፣ በአፈር፣ በድምፅ ብክለቶች ላይ ሰፋፊ ስራዎች እንደሚከናወኑ ገልጸዋል።


 

በንቅናቄው ላይ ለ5ሺህ ነዋሪዎችና ባለድርሻ አካላት ግንዛቤ በመፍጠርና የፕላስቲክ ውጤቶችን መልሶ መጠቀም የሚያስችሉ ስራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ እንደግፋለን ያሉት ደግሞ የድሬዳዋ የአካባቢ፣ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን ስራ አስኪያጅ አቶ አብዱ መሐመድ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም