የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ባለሀብቶች በበጎ ስራዎች ላይ በመሳተፍ ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ባለሀብቶች በበጎ ስራዎች ላይ በመሳተፍ ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቀረበ
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 5/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ባለሀብቶች በበጎ ስራዎች ላይ በመሳተፍ ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቀረበ።
የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የበላይ ጠባቂ አባቶች የኢትዮ-ኢስታንቡል ጠቅላላ ሆስፒታልን እና የሰንሻይን ፊላንትሮፊ ፋውዴሽን የአረጋውያን መጦሪያና መንከባከቢያ ማእከልን ጎብኝተዋል።
በመርሃ-ግብሩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼኽ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ፣ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ ሱራፌል፣ የኢትዮጵያ የወንጌል አማኞች አብያተ ክርቲያናት ጽህፈት ቤት ኃላፊ መጋቤ ጌትነት ለማና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
የበላይ ጠባቂ አባቶች ተዘዋውረው በተመለከቷቸው በጎ ስራዎች መደሰታቸውን እንዲሁም ለሌሎች አካላት ትምህርት የሚሰጡ መሆናቸውን ገልጸው በበጎ ተግባራት የተሳተፉ አካላትን አመስግነዋል።
የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ፀሐፊ ሊቀ ትጉሐን ቀሲስ ታጋይ ታደለ፥ በበጎ አድራጊ ባለሃብቶች የተሰሩ በጎ ስራዎች በጣም የሚያስደስቱ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ምንም ገቢ የሌላቸው አቅመ ደካሞችን ከማገዝ አኳያ ሌሎች ባለሀብቶችን ለመሰል ዓለማ የሚያነሳሳ መሆኑን ጠቁመዋል።
እርስ በርስ መረዳዳትን እና አቅመደካሞችን ማገዝን በተግባር የምናሳይባቸው ተጨማሪ ማእከሎች እንደሚያስፈልጉ ከጉብኝቱ መረዳታቸውን አንስተዋል።
ኢትዮጵያ በብዙ ሺህ ዓመታት የመጣችበት መንገድ በመደጋገፍ እና በመረዳዳት መሆኑን ተናግረዋል።
ባለሃብቶቹ እያከናወኑት ያለው ስራ ይበል የሚያሰኝ መሆኑን ገልጸው መንግስት እንደዚህ አይነት ቅን ሀሳብ ያላቸው የሀገር አለኝታዎች እንዲበራከቱ መደገፍ አለበት ብለዋል።
ባለሀብቶችም የተሰማሩበትን ሀብት መፍጠሪያ ለማሳደግ ከሚያደርጉት ፉክክር ባለፈ በበጎ ስራዎች በመሳተፍ ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን መወጣትና መተባበር እንዳለባቸው ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮ-ኢስታንቡል ጠቅላላ ሆስፒታል ባለቤት እና ዋና ሥራ አስኪያጅ ብርሃን ተድላ፤ ሆስፒታላቸው ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ለመጡ የልብ ችግር ላለባቸው ህፃናት ነፃ የልብ ሕክምና እየሰጠ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
በየዓመቱም 300 የልብ ችግር ያለባቸውን ህጻናት በነጻ ለማከም አቅዶ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፥ ባለፈው አንድ ወር ስድስት ህጻናት ታክመው መዳናቸውን ተናግረዋል።
በህክምናው መስክ የተሰማሩ ባለሀብቶችም አቅማቸው በፈቀደ መጠን በተመሳሳይ በጎ ስራ በመሳተፍ መንግስትን ማገዝ እና የሀገርን ችግርም መፍታት እንደሚገባቸው ጠቁመዋል።
የሰንሻይን ፊላንትሮፊ ፋውንዴሽን መስራችና የሰንሻይን ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሳሙኤል ታፈሰ ሰንሻይን ከኢንቨስትመንት ስራው ጎን ለጎን ማህበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ትምህርት ቤቶችን በመገንባት ዜጎች የትምህርት አገልግሎት እንዲያገኙ እያደረገ ነው ብለዋል።
በአዲስ አበባ በ30 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ በ630 ሚልዮን ብር የሰንሻይን ፊላንትሮፊ ፋውዴሽን የአረጋውያን መጦሪያና መንከባከቢያ ማዕከል ተገንብቶ ወደ ስራ መግባቱን ጠቅሰው፥ ማዕከሉ በራሱ ገቢ እንዲተዳደር የገቢ ማመንጫ ስራዎችን እንደጀመረ ተናግረዋል።
ፋውንዴሽኑ በቀጣይም አቅመ ደካሞችን የመጦር እና የመደገፍ ስራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
ሁሉም ባለሃብቶች በበጎ ስራዎች ላይ በጋራ በመሳተፍ በኢትዮጵያ የሚስተዋሉ ማህበራዊ ችግሮችን ለመቅረፍ እንዲነሱም ጥሪ አቅርበዋል።