የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አመራርና አባላት ለታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከ254 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ አድርጓል - ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አመራርና አባላት ለታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከ254 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ አድርጓል - ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 5/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አመራርና አባላት ለታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከ254 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ ማድረጉን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ገለጹ።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት 13ኛ ዓመት መከበርን ምክንያት በማድረግ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ገቢ ማሰባሰቢያ ዋንጫን ለአዲስ አበባ ፖሊስ አስረክቧል፡፡
በርክክብ መርሃ-ግብሩ ላይ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል መልዕክት አስተላልፈዋል።
በመልዕክታቸውም እያንዳንዱ አመራርና አባላት ከደመወዛቸው፣ በቦንድ ግዥ እንዲሁም በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ገቢ ማሰባሰቢያ የሰላም ዋንጫን ጨምሮ በአጠቃላይ 254 ሚሊየን 41 ሺህ 729 ብር ከ86 ሳንቲም በመሰበሰብ ገቢ አድርገናል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በመላ ሀገራችን የህዝባችንን ሰላምና ደህንነት በማረጋገጥ፤ የመሰረተ ልማት አውታሮችን እና የተጀመሩ ከፍተኛ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን ከአሸባሪዎችና ከፀረ ሰላም ኃይሎች ጥቃት ከመጠበቅ ባሻገር ከኢ.ፌ.ዲ.ሪ መከላከያ ሠራዊትና ከሌሎች የፀጥታና ደህንነት አካላት ጋር በመቀናጀት በሚያከናውናቸው ተግባራት የህይወት መስዋዕትነት ጭምር እየከፈለ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡
የፈጥኖ ደራሽ ኃይላችን የህዳሴ ግድብ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ጉባ መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም የመሠረት-ድንጋይ ከመቀመጡ በፊት ጀምሮ ምንም የተመቻቸ ሁኔታ ባልነበረበት ጫካ መንጥሮ የሣር ጎጆ በመቀለስ አስቸጋሪውን የአየር ፀባይ ተቋቁሞ የግድቡን ግንባታ ፍፃሜ በጉጉት እየተጠባበቀ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡
ለግድቡ ግንባታም እያንዳንዱ አመራርና አባላት ከደመወዛቸው፣ በቦንድ ግዥ እንዲሁም በታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ገቢ ማሰባሰቢያ የሰላም ዋንጫን ጨምሮ በአጠቃላይ 254 ሚሊየን 41 ሺህ 729 ብር ከ86 ሳንቲም በመሰበሰብ ገቢ መደረጉን ገልጸዋል፡፡
ኮሚሽነር ጀነራሉ ወደፊትም ግድቡ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ከወር ደመወዝ በሙሉ ፈቃደኝነት አስተዋጽኦ እንደምናደርግና በግድባችን ላይ አንዳች አደጋ እንዳይደርስ ከኢ.ፌ.ዲ.ሪ መከላከያ ሠራዊት፣ ከሌሎች የፀጥታ እና ደህንነት አካላት ጋር በመቀናጀት ወቅቱ የሚጠይቀውን መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆናችንን በድጋሚ ለመግለጽ እወዳለሁ ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስም እንደ ኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ሁሉ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ገቢ በማሰባሰብ የራሱን አሻራ እያኖረ የሚገኝ ተቋም መሆኑም ተመላክቷል።
የተረከበውን የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የገቢ ማሰባሰቢያ ዋንጫ በየሥራ ክፍሉ በማዘዋወር እንደተለመደው የራሱን አስተዋጽኦ ያበረክታል የሚል እምነት አለኝ ሲሉም ገልጸዋል፡፡
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አረጋዊ በርሄ በበኩላቸው የኢ.ፌ.ዲ.ሪ መከላከያ ሠራዊትና የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ለሀገር አንድነትና ሉዓላዊነት ከሚከፍሉት መስዋዕትነት ባሻገር የሀገራችንን ልማት እና የኢኮኖሚ ነፃነት ለማረጋገጥ ከመላው ህዝብ ጎን በመቆም የሚጠበቅባቸውን ሁሉ እየተወጡ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ መከላከያ ሠራዊት እና የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የግድቡ ግንባታ ከተበሰረበት ዕለት ጀምሮ ባለፉት 13 ዓመታት ታላቅ ብሄራዊ ኩራታችን የሆነውን የህዳሴ ግድብ ከውስጥ ተላላኪ ባንዳዎች እና ከውጭ ጣልቃ-ገብ ጥቃቶች በጽናት በመጠበቅ ፕሮጀክቱ በአስተማማኝ ደህንነት እንዲከናወን አድርገዋል ብለዋል፡፡
ሠራዊቱ ለግድቡ ግንባታ የወር ደመወዙን ለሰባተኛ እና ስምንተኛ ዙር በመስጠት ላለፉት 13 ዓመታት በግንባታው ላይ አሻራውን በደማቅ እያኖረ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ መከላከያ ሠራዊት እና የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የሰላም ዋንጫውን ከዕዝ ወደ ዕዝ እንዲሁም በየጠቅላይ መምሪያዎች በማዘዋወር በደመወዛቸውና በሙያቸው እያደረጉ ካሉት ድጋፍ በተጨማሪ በግንባር ቀደምነት በመሰለፍ በዋንጫው ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ድጋፍ ማድረጋቸውንም አስታውቀዋል፡፡
የሰላም ዋንጫን ከኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የተረከበው የአዲስ አበባ ፖሊስም በጥሩ ንቅናቄ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል እንደሚያምኑ መግለጻቸውን ከኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡