የአገራዊ ምክክሩ ሂደቱ ተሳታፊዎች ሀገራዊ መግባባት በሚፈጥሩ ጉዳዮች ላይ በማተኮር ሃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው - ኮሚሽኑ

572

ሻሸመኔ፤ ሚያዝያ 5/2016(ኢዜአ)፦ በአገራዊ ምክክር ሂደቱ የሚሳተፉ የህብረተሰብ ተወካዮች ሀገራዊ መግባባት በሚፈጥሩ ጉዳዮች በማተኮር ሃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸው የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስገነዘበ።

ኮሚሽኑ በኦሮሚያ ክልል ሻሸመኔ ከተማ ከባሌ ዞን 11 ወረዳዎች ከተውጣጡ የህብረተሰብ ክፍሎች ውስጥ  በአጀንዳ ልየታው የሚሳተፉ 176 ተወካዮችን አስመርጧል።


 

ኮሚሽነር ዶክተር አምባዬ ኦጋቶ በዚህ ጊዜ እንደገለጹት ኮሚሽኑ አካታች፣ አሳታፊና ግልጽነት የተሞላ የአሰራር ስርዓት በመዘርጋት ህዝቡ በሀገሩ ጉዳይ በባለቤትነት እንዲሳተፍ እየሰራ ነው።

መሰረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የሚታዩ አለመግባባቶችን ለመፍታት ሀገራዊ ምክክር ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አስታውሰው፤ በምክክር ሂደቱ የሚሳተፉ የህብረተሰብ ተወካዮች ሀላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ አሳስበዋል።

በተለያዩ ክልሎች በአጀንዳ መረጣ የሚሳተፉ የህብረተሰብ ክፍሎች መረጣ በተሳካ ሁኔታ እየተካሄደ መሆኑንም ገልጸዋል።

በኦሮሚያ ክልልም በአራት ክላስተሮች በአጀንዳ ልየታ የሚሳተፉ የህብረተረሰብ ተወካዮችን የመምረጥ ሂደት እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፤ በእስካሁኑ ሂደትም በ282 ወረዳዎች 5ሺህ 94 የህብረተሰብ ተወካዮች መመረጣቸውን ጠቅሰዋል።

ኮሚሽነር ዶክተር ዮናስ አዳዬ በበኩላቸው የምክክር መድረኩ በህዝቡ ባለቤትነት የሚመራ በመሆኑ በየደረጃው በአጀንዳ ልየታው የሚሳተፉ የህብረተሰብ ተወካዮች ተሳትፎ ድርሻው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።

በአገሪቱ በውይይት ችግሮችን ለመፍታት ኮሚሽኑ የያዘውን የሰላም አማራጭ ከግብ ለማድረስ ሁሉም መተባበር አለበት ብለዋል።

በመድረኩ ከተሳተፉት መካከል ከባሌ ሮቤ የመጡት አባገዳ መለሰ ረታ፣ ኮሚሽኑ ለሀገር ሰላም፣ አንድነትና ልማት የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደሆነ መገንዘባቸውን ተናግረዋል።

ሰላምና ልማትን ማወጅ የአባገዳዎች ፍላጎት መሆኑን ገልጸው ''አለመግባባቶችን በውይይት ለመፍታት ኮሚሽኑ ያስቀመጠው አሰራር ተገቢ ነው'' ብለዋል።

ለኮሚሽኑ ስራ ውጤታማነትም ህዝቡን በማስተባበርና ጠቃሚ አጀንዳዎችን በመስጠት ሃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።

ሌላኛው ወጣት መሃመድ አማኑ በበኩሉ፤ እንደ ሀገር የሚያጋጥሙ ችግሮች በውይይትና ምክክር መፈታት አለባቸው ብሏል።

ወጣቶችንን ወክሎ በተሳታፊ ልየታው መገኘቱን ጠቅሶ፤ ለምክክር ኮሚሽኑ ስኬታማነት የድርሻውን እንደሚወጣ ገልጿል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም