ተማሪዎች በስፔስ ሳይንስ ላይ ያላቸውን እውቀት ለማጎልበት  እየሰራ መሆኑን  የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንሰ  ሶሳይቲ ገለጸ

757

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 5/2016(ኢዜአ)፦ ተማሪዎች በስፔስ ሳይንስ ላይ ያላቸውን እውቀት ለማጎልበት  እየሰራ መሆኑን  የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንሰ  ሶሳይቲ ገለጸ።

የሩሲያ የሳይንስና ባህል ማዕከል ከኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ ጋር በመተባበር ዩሪ ጋጋሪ በሚያዚያ 4 ቀን 1953 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ጠፈር በመንኮራኩር የመጠቀበትን ቀን መታሰቢያ በተለያዩ መርሀ ግብሮች አክብረዋል።

ዩሪ ጋጋሪ በሳይንሱ ዘርፍ ለዓለም ያበረከተውን አስተዋጽኦ የሚያሳዩ ፕሮግራሞች የቀረቡ ሲሆን የጥያቄና መልስ ውድድርም ተካሂዷል።

የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ ስራ አስኪያጅ ብሩክ ተረፈ ማህበሩ በተለያዩ ትምህርት ቤት የሚገኙ ተማሪዎች  በስፔስ ሳይንስ ላይ ያላቸውን እውቀት ለማጎልበት  እየሰራ ነው ብለዋል።

በተለይም ተማሪዎች ልዩ ልዩ የስፔስ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂን በመጠቀም እንዲሁም መርሐግብሮችን በማዘጋጀት ግንዛቤ  እያስጨበጠ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በክረምት ወቅት ተማሪዎች ያላቸውን የእረፍት ጊዜ  በመጠቀም የስፔስ ሳይንስ እውቀታቸውን የሚያሰፉ ስልጠናዎችን እንደሚሰጥም ጠቁመዋል።

የሩሲያ የሳይንስና ባህል ማዕከል ዳይሬክተር አሌክሳንደር ኤቭስቲግኔቭ በበኩላቸው፥ ማዕከሉ ዩሪ ጋጋሪ ወደ ጠፈር የመጠቀበትን ቀን ስለ ስፔስ ሳይንሰ ግንዛቤ በሚፈጥር መልኩ በየዓመቱ ያከብረዋል ብለዋል።



በኢትዮጵያ እና በሩሲያ መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር የሚያከናውናቸውን ተግባራት አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።

በተለይም የሳይንስና ባህል ትውውቅና  ሽግግርን ለማጎልበትም ኢትዮጵያውያን በሩሲያ ነጻ የትምህርት እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ሲሰራ መቆየቱንም ተናግረዋል።

ከዚህም ባሻገር በማእከሉ  በተለያየ ጊዜያት ኪነጥበባዊ ሁነቶችን እያዘጋጀ የባህል ትስስርን ለማጠናከር በመስራት ላይ መሆኑን አመላክተዋል።


 

ዩሪ ጋጋሪ ሚያዚያ 4 ቀን 1953 ዓ.ም ቮስቶክ-1 በተሰኘች መንኮራኩር ወደ ጠፈር በመምጠቅ በሰው ልጅ ታሪክ የመጀመሪያው ሰው ነው።

መንኮራኩሯ  መሬትን በሰዓት 27 ሺህ 400 ኪሎ ሜትር የዞረች ሲሆን፥ ለ108 ደቂቃዎችም  መብረሯን የናሳ መረጃ ያሳያል።

ዩሪ ጋጋሪ በዚህ ድንቅ ስራውም ስሙ በዓለም የናኘ ሲሆን፥ የተለያዩ ሜዳሊያዎችን፣ የክብር ስሞችንና የሶቪየት ህብረት ጀግና ሽልማትን ተቀዳጅቷል።
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም