በአፋር ክልል የወጣቶች ምክር ቤት ተመሰረተ

575

ሰመራ፤ ሚያዚያ 5/2016(ኢዜአ)፦ በአፋር ክልል የወጣቶች ምክር  ቤት ዛሬ በይፋ ተመሰረተ።

ዛሬ በተከናወነው የምስረታ ስነ- ስርዓት የምክር ቤት አባላትና ስራ አስፈፃሚዎች ተመርጠዋል።

በስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ ወይዘሮ የሺ ወርቅ አየነ እንዳሉት፤ በክልል ደረጃ  የወጣቶች ምክር ቤት መመስረቱ የሚበረታታ ነው።


 

አደረጃጀቱም ከተናጠል ይልቅ በጋራ መንቀሳቀስ ለውጤት እንደሚያበቃ አመልክተው፤ አሳታፊና አካታች በሆነ መንገድ የወጣቱን ድምፅና መብት ማስከበር እንደሚገባ ጠቁመዋል።

"አደረጃጀቱ ወጣቶች ያላቸውን አቅም እንዲጠቀሙና ራሳቸውን አብቅተው አገራቸውንና ራሳቸውን መጥቀም የሚችሉበት ነው" ያሉት ደግሞ የክልሉ የወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ሃላፊ አቶ ኡመር ኑሩ ናቸው። 


 

ለወጣቶች ሁለንተናዊ መብት መከበር ምክር ቤቱ  የሚያደርገውን ጥረት እንደሚደግፉ ተናግረዋል።

የክልሉ  ወጣቶች ምክር ቤት ፕሬዚዳንት በመሆን የተመረጠው ኢንጂነር ኢብራሂም መሐመድ ሙሳ ፤ ለወጣቱ ሁለንተናዊ መብት መከበር ምክር ቤቱ ያለሰለሰ ጥረት ያደርጋል ብሏል።


 

ምክር ቤቱ 14 የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላትን ሰይሟል። 

የምክር ቤቱን ምስረታ መርሃ ግብር ያሰናዱት  የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ሚኒስቴር ከአፋር ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ እና ከኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት በጋራ መሆኑን በስነ-ስርዓቱ ላይ ተገልጿል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም