ቤተክርስቲያኗ የውሃ ፓምፖችና ጀኔሬተሮች ለዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ድጋፍ አደረገች - ኢዜአ አማርኛ
ቤተክርስቲያኗ የውሃ ፓምፖችና ጀኔሬተሮች ለዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ድጋፍ አደረገች
ሰቆጣ ፤ ሚያዚያ 5 /2016 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስትያን ከ29 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያላቸው የውሃ ፓምፖችና ጀኔሬተሮች ለዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ድጋፍ አደረገች።
በርክክቡ ወቅት በቤተክርስቲያኗ የባህር ዳር ደሴ ካቶሊክ የልማት ማስተባበሪያ ቢሮ የዋሽ ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ደጀን ይግዛው እንዳሉት፤ በውሃ ፣ በጤና እና በትምህርት ዘርፎች መንግስት የሚያካሄደውን ልማት ቤተክርስቲኗ ለመደገፍ እየሰራች ነው ።
በዚህም በብሄረሰብ አስተዳደሩ በነበረው ችግር ጉዳት የደረሰባቸውን የውሃ ተቋማት ወደ ቀደመ አገልግሎታቸው ለመመለስ የሚያስችሉ የተለያዩ ቁሳቁሶችን ድጋፍ መደረጉን ተናግረዋል።
ዛሬ በተደረገው ድጋፍም 29 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው ሰባት የውሃ መግፊያ ፓምፖች፤ ሦስት ጀነሬተሮች እና ሌሎችንም ቁሳቁሶች ያካተተ መሆኑ ጠቅሰዋል።
ቁሳቁሶች ወደ አገልግሎት እንዲበቁም አስፈላጊውን ስልጠና እንደሚሰጥ ጠቁመው፤ በቀጣይም ለአርሶ አደሩ የምርጥ ዘር ድጋፍ ለማድረግ ዝግጅት መደረጉን አመልክተዋል።
የብሄረሰብ አስተዳደሩ የውሃና ኢነርጂ መምሪያ ሃላፊ አቶ አብርሃም አሰፋ በበኩላቸው፤ የቤተክርስቲያኗ ድጋፍ የሰቆጣ ከተማን ጨምሮ በሰቆጣ ወረዳ ሁለት ቀበሌዎች ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን የንፁህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
ድጋፉ የጀኔሬተርና የውሃ መግፊያ ፓምፖች በተጨማሪ በከተማና በገጠር የሚገኙ የውሃ ተቋማትን የውሃ ጥራት መመርመሪያ መሳሪያን ጨምሮ የውሃ ማከሚያ ኬሚካል ያካተተ መሆኑን አረጋግጠዋል።
ከነገ ጀምሮ ወደ ስራ እንዲገቡም ይደረጋል ብለዋል።
የዋግ ልማት ማህበር ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር ሃይሌ ወልዴ ፤ የውሃ መሰረተ ልማቶችን መልሶ ለማቋቋም የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ላደረገችው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።