ቀጥታ፡

በብሔራዊ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት 14 ሚሊዮን ወጣቶችን በማሳተፍ ለሀገር ግንባታና ለማህበረሰቡ የሚጠቅሙ ተግባራት ተከናውነዋል

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 5/2016(ኢዜአ)፦ በብሔራዊ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት 14 ሚሊዮን ወጣቶችን በማሳተፍ ለሀገር ግንባታና ለማህበረሰቡ የሚጠቅሙ ተግባራት መከናወናቸውን የሰላም ሚኒስቴር አስታወቀ።

ብሔራዊ የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን ይበልጥ ለማጠናከርና ዘላቂ ለማድረግ የወጣቶች በጎ ፈቃድ ማህበር መዋቅርና ራሱን የቻለ አሰራር እየተዘጋጀ መሆኑንም ገልጿል።

በሰላም ሚኒስቴር የብሔራዊ በጎ ፈቃድ አገልግሎት መሪ ስራ አስፈፃሚ ገመቺሳ ቲቻ ለኢዜአ እንደገለጹት ብሔራዊ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሀገራዊ መግባባት መፍጠርና ዘላቂ የሰላም ግንባታን ማጠናከር ላይ ወጣቶች አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ የማድረግ ዓላማ ይዞ በ2013 ዓ.ም ተጀምሯል።

ወጣቶች በድንበር ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ ስራዎች በመሳተፍ ከማህበረሰቡ ጋር ትስስር እንዲፈጥሩ፣ ህብረ ብሔራዊ አንድነትንና አብሮነትን እንዲያጠናክሩ አበርክቶ ያለው መሆኑንም ገልፀዋል።

እስካሁን በስምንት ዙር ወጣቶችን በማሰልጠን በርካታ ውጤቶች መገኘታቸውን ጠቅሰው፥ ለአብነትም ወጣቶች ለብሔራዊ መግባባት ሚናቸውን እንዲወጡና የሀገር ፍቅር ስሜታቸው እንዲጎለብት ማስቻሉን አስረድተዋል።

ከዚህም ባለፈ ለበጎ ፈቃድ ስራ በሄዱባቸው አካባቢዎች የንግድ ስራ የጀመሩ ወጣቶች መኖራቸውንም ገልጸዋል።

ወጣቶቹ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ትልቅ ሚና እየተጫወቱ ነው ያሉት አቶ ገመቺሳ፥ ማህበራዊ ችግሮችን የሚፈቱና ማህበረሰቡን የሚጠቅሙ አገልግሎቶችን እየሰጡ እንደሚገኙም አንስተዋል።

ሚኒስቴሩ በዚህ ዓመት ብቻ ዓድዋን ለዘላቂ ሰላምና ለሀገር ግንባታ በሚል ባዘጋጃቸው መድረኮች 5 ሚሊዮን ወጣቶች መሳተፋቸውንም ተናግረዋል።

በብሔራዊ በጎ ፈቃድ አገልግሎት እስካሁን 14 ሚሊዮን ወጣቶችን በማሳተፍ ለሀገር ግንባታ እና ለማህበረሰቡ የጎላ ፋይዳ ያላቸው ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።

የሀገር ግንባታና የዘላቂ ሰላም ስራ በትውልድ ቅብብሎሽ የሚፈጸምና ቀጣይነት ያለው በመሆኑ ብሔራዊ የበጎ ፈቃድ ስራን ዘላቂ ለማድረግ ወደ ተግባር መገባቱን አመላክተዋል።

ለዚህም የኢትዮጵያ ወጣቶች የበጎ ፈቃድ ማህበር እየተዋቀረ መሆኑን ገልጸው፥ እስካሁንም የ34 ሺህ አባላት ምዝገባ መከናወኑን ጠቅሰዋል።

ለበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ የአሰራር ስርዓት እየተዘጋጀ ሲሆን ወጣቶች መረጃ የሚለዋወጡበት ዲጂታል ስርዓትም ወደ ስራ ገብቷል ብለዋል።

በዚህም ወጣቶች በጎ ፈቃደኝነትን የህይወት ዘመን ስራቸው በማድረግ ለሌሎችም አርዓያ እንደሆኑ ግብ መቀመጡን ተናግረዋል።

አቶ ገመቺሳ አክለውም የዘጠነኛ ዙር የብሔራዊ በጎ ፈቃድ አገልግሎት ስልጠና በመጪው ሳምንት እንደሚጀመር ጠቅሰው፥ በስልጠናውም 1ሺህ 500 ወጣቶች እንደሚሳተፉ ተናግረዋል።

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተጠናክሮ እንዲቀጥል መንግስት እያደረገ ያለውን ጥረት መንግስታዊ ያልሆኑ አካላትና ህብረተሰቡ እንዲደግፍም ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም