የሰሜን ምዕራብ ዕዝ ኮር ያሰለጠናቸውን ወታደራዊ ፖሊስ አባላትን አስመረቀ

606

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 5/2016 (ኢዜአ) የሰሜን ምዕራብ ዕዝ ኮር ያሰለጠናቸውን የኮር እና የክፍለ ጦር ወታደራዊ ፖሊስ አባላትን አስመርቋል።

የኮሩ ዋና አዛዥ ብርጋዲየር ጄኔራል ወርቅነህ ጉደታ የወታደራዊ ፖሊስ ስልጠናን አጠናቃችሁ የተመረቃችሁ የደጀን ጥበቃ የሰራዊት አባላት ጠንካራ ስልጠናዎችን በብቃት ተወጥታችሁ ለምረቃ መብቃታችሁ የጥንካሬያችሁ ማሳያ ነው ብለዋል።

ተመራቂዎች በቀጣይም ወታደራዊ ደንቦችንና ስርዓትን ማስከበር እንዲሁም በኮማንድ ፖስቱ የተቀመጡ ተልዕኮዎችን በድል መፈፅም ይጠበቅባችኋል ሲሉ ጄኔራል መኮንኑ አሥገንዝበዋል።


 

አሁን ላይ በአካላዊ ጥንካሬ ፣ በስነ-ልቦና እና በወታደራዊ ሳይንስ የበቃ ጊዜን እና ቴክኖሎጂን በአግባቡ የሚጠቀም የሰው ሃይል እያሰለጠን እንገኛለን ያሉት ብርጋዲየር ጄኔራል ወርቅነህ ጉደታ ሰራዊቱ በፅንፈኞችና በፀረ-ሰላም ሀይሎች ላይ እርምጃ እየወሰደ የሰላም ችግር የነበረባቸው አካባቢዎች ወደ ቀደመ ሰላማቸው እንዲመለሱ በማድረግ የተሰጠውን ግዳጅ በድል እየተወጣ መሆኑን አስረድተዋል።


 

የስልጠናውን ሪፖርት ያቀረቡት ሻምበል አሰፋ ቅጣው ፤ የወታደራዊ ፖሊስ ሥልጠና የወሠዱ የደጀን ጥበቃ አባላት በሰልጠና ቆይታቸው ፈታኝ በሆነ የአየር ንብረት ሁሉንም የመሬት ገፅ በማስተዋወቅ በቀጣይ የሚሰጣቸውን ግዳጅ በአጭር ጊዜ በዲሲፒሊን እና በሃላፊነት በብቃት የሚወጡበት አቅም መጨበጣቸውን ገልፀዋል።

የወታደራዊ ፖሊስ ስልጠና ከወሰዱ የደጀን ጥበቃ አባላት እና አሰልጣኞች መካከል አስር አለቃ ደረጀ ደምሴና ምክትል አስር አለቃ አበራሽ መከበ ስልጠናው ውስብስብ ግዳጆችን በጥበብና በጀግንነት እንዲወጡ አይነተኛ ሚና መኖሩን ገልፀው ከስልጠናው አካላዊና አእምሯዊ ብቃት እንዳገኙ መግለጻቸውን ከመከላከያ ሰራዊት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ቀጣይም የሚሰጣቸውን ግዳጅ በአግባቡ ለመፈፀም ዝግጁ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም