በፓሪስ ኦሎምፒክ ውድድር  ኢትዮጵያ የላቀ ውጤት እንድታስመዘግብ ዝግጅት  እየተደረገ  ነው

809

ደሴ ፤ሚያዝያ 5 /2016(ኢዜአ)፡-  በፈረንሳይ ፓሪስ በሚካሄደው የኦሎምፒክ  ውድድር  ኢትዮጵያ የላቀ ውጤት እንድታስመዘግብ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ  ኦሎምፒክ ኮሚቴ አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ከአማራ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ጋር በመተባበር በደሴ ከተማ  የኦሎምፒክ ችቦ ማብራትና ቅብብሎሽ መርሃ ግብር አካሂዷል፡፡

በኮሚቴው የፓሪስ 2024 ኦሎምፒክ ውድድር የቴክኒክና ህዝብ ግንኙነት ሰብሳቢ አቶ ቢልልኝ መቆያ እንዳመለከቱት፤ በመጪው ሐምሌ ወር የኦሎምፒክ ስፖርት ውድድር በፓሪስ ይካሄዳል።

በውድድሩ ኢትዮጵያ የተሻለ ውጤት እንድታስመዘገብ ከወዲሁ የቅድመ ዝግጅት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም በውጭና በአገር  ቤት ህብረተሰቡን የማነቃቃትና ግንዛቤ የመፍጠር፣ ገቢ የማሰባሰብ፣ ስፖርተኞችን የመመልመል፣ በክልሎች የችቦ ቅብብሎሽና ሌሎችም ዝግጅቶች በመደረግ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

በውድድሩ ኢትዮጵያ በአትሌቲክስና ውሃ ዋና እንደምትሳተፍ ጠቁመው፤ የላቀ ውጤት በማስመዝገብ ወርቅ ለማምጣትና የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በዓለም አደባባይ ከፍ አድርጎ ለማውለብለብ  እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ስፖርት ለዘላቂ ሰላምና አብሮነትም ከፍተኛ ሚና እንዳለው ጠቅሰው፤ ህብረተሰቡ በስፖርት መተሳሰርና የእርስ በእርስ ግንኙነቱን ማጠናከር እንዳለበት አመልክተዋል፡፡

የአማራ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ እርዚቅ ኢሳ በበኩላቸው፤ በቀጣይ ክረምት በፓሪስ በሚካሄደው ኦሎምፒክ ኢትዮጵያን የሚወክሉ ስፖርተኞችን ለማፍራት ክልሉ የበኩሉን እየሰራ መሆኑን ገለጸዋል፡፡


 

ለዚህም በክልሉ በሚገኙ 16 የአትሌቲክስ ማስልጠኛ ማዕከላት ልዩ ድጋፍና ክትትል እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው፤ በማዕከላቱ በዓለም የውድድር መድረክ መሳተፍ የቻሉ ስመ ጥር አትሌቶችን ማፍራት ተችሏል ብለዋል፡፡

በክልሎች መካከል የችቦ ቅብብሎሽ እየተካሄደ መሆኑም የእርስ በእርስ ግንኙነትን ከማጠናከሩ ባለፈ ስፖርቱን ለማነቃቃትና ብቁ ተወዳዳሪ ለመፍጠር እያገዘ ይገኛል ብለዋል።

ከኦሮሚያ ክልል የተቀበሉትን የኦሎምፒክ ችቦ ዛሬ ለደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል አስረክበዋል፡፡

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ባህል ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ፈንታሁን ብላቴ እንዳሉት፤ በፓሪስ ለሚካሄደው ኦሎምፒክ የሚሳተፉ ብቁ ስፖርተኞችን ለማፍራት በቅንጅት እየተሰራ ይገኛል፡፡


 

የኦሎምፒክ ችቦውን ከአማራ ክልል መረከባቸውን ጠቅሰው፤ በቀጣይ በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች በማዘዋወር ዘርፉን ለማነቃቃትና የህብረተሰቡን አንድነት ለማጠናከር እንሰራለን ብለዋል፡፡

የወሎ ዩኒቨርሲቲ ተወካይ ዶክተር ሙሳ አዳል በበኩላቸው፤ ዩኒቨርሲቲው የስፖርቱን ዘርፍ በመደገፍ የተሻለ ውጤት የሚያስመዘግቡ ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራትም እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ለዚህም የተንታ አትሌቲክስ ማስልጠኛ ማዕከልን ተረክቦ ስመ ጥር አትሌቶችን ከማፍራት ባለፈ በደሴና ኮምቦልቻ ከተሞች 120 ታዳጊዎችን በቋሚነት እያሰለጠነ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል፡፡

በመርሃ ግብሩ የፌዴራል፣ የክልል፣ የወሎ ዩኒቨርሲቲና የደሴ ከተማ አመራር አባላትና የስፖርት ቤተሰቦች ተገኝተዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም