በትግራይ ክልል መቀሌ ከተማ ለሚካሄደው ሀገር አቀፍ የሕብረት ሥራ ማህበራት ባዛርና ኤግዚቪሽን ዝግጅቱ ተጠናቋል - ኢዜአ አማርኛ
በትግራይ ክልል መቀሌ ከተማ ለሚካሄደው ሀገር አቀፍ የሕብረት ሥራ ማህበራት ባዛርና ኤግዚቪሽን ዝግጅቱ ተጠናቋል
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 4/2016(ኢዜአ):- በትግራይ ክልል መቀሌ ከተማ ለሚካሄደው ሀገር አቀፍ የሕብረት ሥራ ማህበራት ባዛርና ኤግዚቢሽን ዝግጅቱ መጠናቀቁን የክልሉ ሕብረት ስራ ማህበራት ኤጀንሲ አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ሕብረት ሥራ ኮሚሽን እና የትግራይ ክልል ሕብረት ሥራ ማህበራት ኤጀንሲ ትብብር ከሚያዚያ 12 እስከ 19 ቀን 2016 ዓ.ም የሚቆይ ሀገር አቀፍ ባዛርና ኤግዚቢቪን በመቀሌ ከተማ ይካሄዳል።
"ሕብር ባዛርና ኤግዚቪን' በሚል መሪ ሃሳብ የሚካሄደውን ይህን ባዛርና ኤግዚቪን አስመልክቶ የሁለቱ ተቋማት የሥራ ኅላፊዎች በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ዝግጅቱ መጠናቀኑን ተናግረዋል።
የትግራይ ክልል ሕብረት ስራ ማህበራት ኤጀንሲ ኅላፊ አቶ ነጋ አሰፋ በባዛርና ኤግዚቪሽኑ ከመላ ሀገሪቷ የተውጣጡ ከ200 በላይ ማኅበራት ምርትና አገልግሎታቸውን ይዘው ይቀርባሉ ብለዋል።
የኢኮኖሚ እንቅስቃሴውን፣ የዘርፉን ለማነቃቃት እና በድርቅና በሌሎች ምክንያቶች በክልሉ የሚስተዋል የምርት አቅርቦት እጥረትን ለማቃለል ያግዛል ብለዋል።
የክልሉ ሕብረት ሥራ ማኅበራት ከሁሉም ክልሎች ከተወጣጡ ሕብረት ሥራ ማኅበራት ጋር የገበያ ትስስርና ዘላቂ የፋይናንስ ግንኙነትን ለማጠናከር ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥርም እንዲሁ።
ለኤግዚቪሽኑ መሳካት ድጋፍ ያደረጉ ባለድርሻ አካላትንም አመስግነዋል።
የኢትዮጵያ ሕብረት ሥራ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ሺሰማ ገብረሥላሴ፤ ከባዛርና ኤግዚቪሽኑ በተጓዳኝ የሕብረት ስራ ዘርፉ ችግሮችና መፈትሔዎች ላይ ያተኮሩ ውይይቶች ይካሄዳሉ ብለዋል።
ሁነቱ ምርጥ ተሞክሮዎች የሚቀርቡበትና የዘርፉ የምርት ቴክኖሎጂዎች የሚተዋወቁበት በመሆኑ ለግብርናው ዘርፍ ማዘመን የሚደረጉ ጥረቶችን እንደሚያግዝም ገልጸዋል።
በመቀሌ የሚካሄደው ሀገር አቀፉ የሕብረት ሥራ ማህበራት ባዛርና ኤግዚቪሽን ከሚያዚያ 12 እስከ 19 ቀን 2016 ዓ.ም የሚካሄድ ይሆናል።