ቀጥታ፡

ኢትዮጵያን ጨምሮ ለተለያዩ የአፍሪካ አገራት ሁሉን አቀፍ የተጠናከረ የልማት ትስስር ድጋፍ ይደረጋል- የአውሮፓ ህብረት

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 4/2016(ኢዜአ):- ኢትዮጵያን ጨምሮ ለተለያዩ የአፍሪካ አገራት ሁሉን አቀፍ የተጠናከረ የልማት ትስስር ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑን የአውሮፓ ህብረት ገለጸ።

በኢትዮጵያ የአውሮፓ ሕብረት አምባሳደር ሮላንድ ኮቢያ እና በአፍሪካ ሕብረት የአውሮፓ ሕብረት አምባሳደር ጃቬር ፔሬዝ በፈረንጆቹ ግንቦት 9 የሚከበረውን የአውሮፓ ቀን አስመልክቶ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

የአውሮፓ ሕብረት አምባሳደር ሮላንድ ኮቢያ በመግለጫቸው ከ74 ዓመታት በፊት ጀምሮ የአውሮፓ ሕብረትን ለመመስረት በጥቂት የአውሮፓ ሀገራት መካከል የትብብር ስምምነት መደረጉን አስታውሰዋል።


 

በዚህም የአውሮፓ ሕብረት የነፃ ፓስፖርት ዝውውርና የጋራ መገበያያ ገንዘብ የመጠቀም ትግበራን ጨምሮ በሀገራት መካከል ሁለንተናዊ ዘላቂ ትብብር የፈጠረበት ደረጃ ላይ ደርሷል ብለዋል።

የአውሮፓ ሕብረት ኢትዮጵያን ጨምር ከተለያዩ አገራት ጋር በዘላቂና መርህ መር አግባብ የትብብር ግንኙነቱን አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያ ሕብረቱ ከመሰረታቸው ወሳኝ ስትራቴጂካዊ አጋር ሀገራት መካከል አንዷ መሆኗን ጠቅሰው፣ በፖለቲካና ኢኮኖሚ መስኮች ጠንካራ ትብብር መመስረታቸውን አንስተዋል።

ሰላምና መረጋጋት፣ በማህበራዊ ጥበቃ እና ምጣኔ ሀብት ወሳኝ የትብብር መስኮች መሆናቸውን ጠቅሰው፤  በትምህርትና ጤና ፕሮጀክቶችም ተጨባጭ ለውጥ ያመጡ ውጤቶች እንደተመዘገቡ ተናግረዋል።

በርካታ አስርት ዓመታትን ባስቆጠረው የኢትዮጵያና የአውሮፓ ሕብረት ትብብር በኢኮኖሚና ንግድ ግንኙነት በተለይም የግሉ ዘርፍ ማጎልበት የሚያስችሉ ስራዎች እንደተከናወኑ ገልጸዋል።

አውሮፓ 20 በመቶ የኢትዮጵያ ኤክስፖርት መዳረሻ እንዲሁም ሁለተኛው የኢትዮጵያ ገቢ ምርቶች (ኢምፖርት) ምንጭ መሆኑንም ለአብነት አንስተዋል።

አሁንም በሁለቱም ወገኖች በኩል ወሳኝ የትብብር መስኮች እንዳሉ የጠቆሙት አምባሳደሩ፤ ይህን ዕምቅ አቅም በመጠቀም የጋራ ፍላጎቶችን ለማሳካት የሁለቱንም ወገኖች ቁርጠኝነት ይጠይቃል ብለዋል።


 

በአፍሪካ ሕብረት የአውሮፓ ሕብረት አምባሳደር ጃቬር ፔሬዝ፤ የአውሮፓ ሕብረትና አፍሪካ በኢኮኖሚ፣ በሰላም መረጋጋት እንዲሁም በሰው ተኮር የልማት ስራዎች በትብብር እየሰሩ መሆኑን ገልፀዋል።

በንግድና ኢንቨስትመንት ረገድም የአውሮፓ ሕብረት አባል ሀገራት ኩባንያዎች ከ241 ቢሊዮን ዩሮ በላይ ኢንቨስትመንት እንዳላቸው ጠቅሰዋል።

በሰላምና መረጋጋት፣ በስደት እና በሌሎች የባለብዙ ወገን ትብብር መስኮችም በጋራ እየሰሩ ስለመሆኑ አንስተው ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያን ጨምሮ ለአፍሪካዊያን ሁሉን አቀፍ ትስስርና ልማት ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል።

የአፍሪካ የነጻ ንግድ ቀጣና እንዲቀላጠፍና ሀገራት በሃይል፣ በመንገድ፣ በአቪዬሺን እና በሌሎች የመሰረተ ልማት መስኮች እንዲተሳሰሩ እገዛና ድጋፉ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም