የብሔራዊ ዘላቂ ኢነርጂ ልማት ስትራቴጂ ወጥ የኢነርጂ አሰራር ስርአት ለመፍጠር ወሳኝ ነው - የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር

691

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 4/2016(ኢዜአ)፦የብሔራዊ ዘላቂ ኢነርጂ ልማት ስትራቴጂ  ወጥ የኢነርጂ አሰራር ስርአት ለመፍጠርና የኢነርጂ ሃብትን በአግባቡ ለመጠቀም ወሳኝ መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ገለጸ።

የኢነርጂ ልማት ስራ ወጥነት ባለው መልኩ እንዲተገበርና የኢነርጂ ተደራሽነትን ለማስፋት ስትራቴጂው ወሳኝ ሚና እንዳለው ተገልጿል።

የብሔራዊ ዘላቂ ኢነርጂ ልማት ስትራቴጂ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በዛሬው እለት ይፋ የተደረገ ሲሆን ስትራቴጂውን የተመለከተ አውደ ጥናትም ተካሄዷል።


 

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ኢንጂነር ሱልጣን ወሊ፤ በስትራቴጂ የታገዘ ዘላቂ የኢነርጂ አጠቃቀምን መከተል አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

የኃይል ምንጮችን መጠቀም ለዘላቂ የኢነርጂ ልማት እውን መሆን ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው ለዘርፉ ስራ ከፍተኛ የኢንቨስትመንት ያስፈልጋል ብለዋል።

በመሆኑም በዘርፉ ያሉ እድሎችንና አማራጮችን ከግምት ውስጥ በማስገባት የብሔራዊ ዘላቂ ኢነርጂ ልማት ስትራቴጂ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎትና የነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን የተወጣጣ የባለሙያዎች ቡድን ስትራቴጂውን ለማዘጋጀት 1 ዓመት ከ6 ወር ጊዜ የወሰደ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የኢነርጂ ፖሊሲ መሬት ወርዶ በሚፈለገው ደረጃ እንዲተገበር፣ የኢነርጂ ሀብቶችን በተመለከተ የተቀናጀ መረጃ ለመስጠትና የግሉ ዘርፍ ያለውን ድርሻ ለማሳደግ ስትራቴጂው የላቀ ጠቀሜታ ይኖረዋል ብለዋል።

በተበታተነ መልኩ ይተገበር የነበረውን የኢነርጂ የአሰራር ማዕቀፍ ወጥነት እንዲኖረው የሚያስችል መሆኑንም ገልጸዋል።

ከዚህ በፊት ስትራቴጂውን የተመለከቱ ስድስት የግብአት ማሰባሰቢያ መድረኮች መካሄዳቸውን አስታውሰው የአሁኑ የመጨረሻ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

የስትራቴጂው የማጠናቀቂያ ስራዎች ከተከናወኑ በኋላም በ2017 ዓ.ም መጀመሪያ ላይ ወደ ትግበራ ይገባል ብለዋል። 


 

በኢትዮጵያ የጀርመን ኤምባሲ የኢኮኖሚ ዘርፍ ኃላፊ ሬቤካ አልት፤ የሀገራቸው መንግስት በጀርመን ዓለም አቀፍ የልማት ትብብር ድርጅት (ጂ አይ ዜድ) በኩል ለስትራቴጂው ዝግጅት ድጋፍ ማድረጉን አመልክተዋል።

ለስትራቴጂው መዳበር አውደ ጥናቶች እንዲካሄዱ ማድረግና የአቅም ግንባታ ስራዎችን ጨምሮ የተለያዩ የቴክኒክ ድጋፎችን ማድረጉን አስታውሰዋል።

ጀርመን በኢነርጂው ዘርፍ ለኢትዮጵያ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ የምትቀጥል መሆኑንም ተናግረዋል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የውሃና ኢነርጂ ልማት ቢሮ የአማራጭ ኢነርጂ ጥናት ልማት ክትትል ዳይሬክተር የሱፍ ሙባረክ ስትራቴጂው የኢነርጂ ሃብትን በአግባቡ ለመጠቀም የሚያግዝ መሆኑን ገልጸዋል።

የሶማሌ ክልል ማዕድን ኢነርጂና ነዳጅ ቢሮ የኢነርጂ ዘርፍ ዳይሬክተር መሐሙድ መሐመድ እና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የማዕድንና ኢነርጂ ልማት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ገብረማርያም ሰጠኝ ስትራቴጂው ለዘርፉ ልማትና ተጠቃሚነት ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ሴቶች የኢነርጂ ማህበር ምክትል ፕሬዝዳንት ሊንዳ ላጲሶ፤ የግሉ ዘርፍ በኢነርጂው ዘርፍ ያለውን ተሳትፎ ለማሳደግ እንዲሁም እውቀትና ቴክኖሎጂን ስራ ለማዋል ስትራቴጂው ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

የብሔራዊ ዘላቂ ኢነርጂ ልማት ስትራቴጂ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጠጣር ከ2024 እስከ 2030 ተግባራዊ እንደሚሆን በአውደ ጥናቱ ላይ ተመላክቷል።

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም