የኢትዮጵያ ሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም የእምባ ጠባቂዎች ዕጩ አቅራቢ ኮሚቴ ስራውን ጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም የእምባ ጠባቂዎች ዕጩ አቅራቢ ኮሚቴ ስራውን ጀመረ

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 4/2016(ኢዜአ)፦በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተቋቋመው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም የእንባ ጠባቂዎች ዕጩ አቅራቢ ኮሚቴ ስራውን በይፋ ጀምሯል።
የዕጩ አቅራቢ ኮሚቴው በኢትዮጵያ ሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ዕጩ ምክትል ዋና እንባ ጠባቂና እንባ ጠባቂዎችን ለመመልመል በተዘጋጀው እቅድና የአሰራር መምሪያ ላይ ተወያይቶ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል፡፡
ኮሚቴው እጩዎቹን ለመመልመል በተቀመጡ ዝርዝር መመዘኛዎችና የጥቆማ አቀባበል ሂደቶች ዙሪያ በዝርዝር ከተወያየ በኋላ ነው እቅዱን እና የአሰራር መምሪያውን ያጸደቀው፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ ሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋምን የሚያቋቁሙና ተቋሙን የሚመሩ አባላትን እንዲመረጥና እንዲሰይም እንዲሁም ስልጣንና ተግባራቸውን በህግ እንደሚወስን በተደነገገው አዋጅ መሠረት በምክር ቤቱ የተቋቋመው ዕጩ አቅራቢ ኮሚቴ ግልፅነት በተሞላበት መንገድ በቀረበው የሕዝብ ጥቆማ መሠረት ዕጩዎች ተወዳድረው ለምክር ቤቱ እንዲቀርቡ ይፋ አድርጓል።
የጥቆማ አቀባበል ስነ-ስርዓቱም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሚገኘው የእጩ አቅራቢ ኮሚቴው ጽህፈት ቤት በአካል በመቅረብና በተለያዩ የቴክኖሎጅ መሰረተ-ልማቶች የሚከናወን ነው፡፡
የእጩ አቅራቢ ኮሚቴው አወቃቀርም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ ሰብሳቢ፣ የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር አባል፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ቴዎድሮስ ምህረት አባል፣ ከምክር ቤቱ የተመረጡ አምስት አባላት፣ በምክር ቤቱ መቀመጫ ካላቸው ተፎካካሪ ፓርቲዎች ሁለት አባላት፣ ከንግድ ምክር ቤት የተወከሉ አንድ አባል እና ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት የተወከሉ አንድ አባል በአጠቃላይ 12 አባላትን የያዘ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል፡፡
ኮሚቴው የዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ እውነቱ አለነን ጸሐፊ አድርጎ መምረጡም ተመላክቷል፡፡
የዕጩ አቅራቢ ኮሚቴው ጸሐፊ አቶ እውነቱ አለነ በምክትል ዋና እምባ ጠባቂ እና እምባ ጠባቂዎች ምትክ ዕጩዎች ተወዳድረው ለምክር ቤቱ እንዲቀርቡ መስፈርቶችን ይፋ ማድረጋቸውን ተከትሎ ከሚያዚያ 5 እስከ ሚያዚያ 20 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ ባሉት 15 ቀናቶች ዕጩዎችን መጠቆም እንደሚቻል ገልጸዋል።
በዚህም መሠረት ዕጩ ተጠቋሚ ምክትል ዋና እምባ ጠባቂ እና እምባ ጠባቂዎች ማሟላት ያለባቸውን መስፈርቶች የጠቆሙ ሲሆን ኢትዮጵያዊነት፣ ከማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት ገለልተኛ የሆነ (ነች)፣ በህግ የትምህርት መስክ ከታወቀ ዩኒቨርስቲ የመጀመሪያ ዲግሪ ያለውና በዘርፉ በቂ የስራ ልምድ ያለውና ያላት፣ መልካም ስነምግባር ያለው (ላት)፣ ኃላፊነትን የመሸከም ብቃት ያለው ( ላት)፣ ለህገ መንግስቱ ተገዢ የሆነ ( ነች) እና ከደንብ መተላለፍ ውጪ በወንጀል ተከሶ ያልተፈረደበት የሚሉ መስፈርቶችን የኮሚቴው ሰነድ ይፋ ማድረጉን በምክር ቤቱ በማህበራዊ ትስስር ገጹ አስታውቋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መጋቢት 5 ቀን 2016፣ ዓ.ም በካሄደው 17ኛ መደበኛ ስብሰባው በአዋጅ ቁጥር 1142 / 2011 አንቀፅ 18 እና በተሻሻለው አዋጅ ቁጥር 1307/2016 አንቀፅ 11 መሠረት በውሳኔ ቁጥር 12/ 2016 ዕጩ አቅራቢ ኮሚቴ ማቋቋሙ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተጠሪ ከሆኑ የዴሞክራሲ ተቋማት አንዱ መሆኑ ይታወቃል፡፡