ቀጥታ፡

በሚቀጥሉት ቀናት በአብዛኛው የበልግ ዝናብ ተጠቃሚ ሥፍራዎች የተሻለ እርጥበት ይኖራቸዋል

አዲስ አበባ ፣ሚያዚያ 04/ 2016 (ኢዜአ)፡-በቀጣይ ስምንት ቀናት ዝናብ ሰጪ የሚቲዎሮሎጂ ገፅታዎች በአብዛኞቹ የበልግ ዝናብ ተጠቃሚ የአገሪቱ አካባቢዎች ላይ እየተጠናከሩ እንደሚሄዱ የኢትዮጵያ የሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ገለፀ።

ኢንስቲትዩቱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ፤ ዝናብ ሰጪ የሚቲዎሮሎጂ ገፅታዎች፤ በአብዛኞቹ የበልግ ዝናብ ተጠቃሚ የአገሪቱ አካባቢዎች እየተጠናከሩ እንደሚሄዱ አመላክቷል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘም በደቡብ፣ በደቡብ ምዕራብ፣ በመካከለኛው ምሥራቅና  በስምጥ ሸለቆ አካባቢዎች የተሻለ ጥንካሬ እንደሚኖረውም በትንበያው ተገልጿል። 

በሚቀጥሉት ቀናትም በአብዛኛው የበልግ ዝናብ ተጠቃሚ ሥፍራዎች የተሻለ እርጥበት እንደሚኖራቸውና የግብርና ሥራዎችን ለማከናወን እንደሚጠቅሙ ገልጿል።

ይህም የረዥም ጊዜ ሰብሎችን ለመዝራት፤ በቡቃያና በተለያየ የዕድገት ደረጃ ላይ ለሚገኙ የበልግ ሰብሎችና ለቋሚ ተክሎች የውኃ ፍላጎት መሟላት፤ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ነው የጠቆሙት።

የሚጠበቀው እርጥበታማ ሁኔታ ለእርሻ ሥራ እንቅስቃሴ አመቺ ሁኔታን ስለሚፈጥር አርሶ አደሮች ተገቢ የሆኑ ግብዓቶችን በመጠቀም የእርሻ ሥራቸውን በተሟላ መልኩ ማካሄድ እንደሚገባቸው ገልጿል።

በሚቀጥሉት ቀናት በኦሞ ጊቤ፣ ስምጥ ሸለቆ፤ በላይኛውና በመካከለኛው ባሮ አኮቦ፤ አዋሽ፣ አባይ፣ ገናሌ ዳዋ፣ በመካከለኛው ተከዜ እና በላይኛው ዋቢ ሸበሌ ተፋሰሶች ከፍተኛ የእርጥበት ሁኔታ እንደሚኖር ጠቁሟል።

ከዚህም ጋር ተያይዞ የሚጠበቀው ከፍተኛ እርጥበት፤ ለገፀ ምድርም ሆነ ለከርሰ ምድር ውሃ ኃብት መጎልበት አዎንታዊ ሚና እንደሚኖረው ኢንስቲትዩቱ አስታውቋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም