ቀጥታ፡

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በህብረተሰብ ተሳትፎ የአካባቢ ብክለትን ለመከላከል በትኩረት ይሰራል

ሚዛን አማን ፤ሚያዚያ 4/2016 (ኢዜአ)፦ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የአካባቢ ብክለትን ለመግታት ከኅብረተሰቡ ጋር በቅንጅት እንደሚሠራ የክልሉ ደን፣ አካባቢ ጥበቃና አየር ንብረት ለውጥ ቢሮ አስታወቀ።


ቢሮው "ብክለት ይብቃ ውበት ይንቃ" በሚል መሪ ቃል በአካባቢ ጥበቃ ሥራ ላይ ግንዛቤ መፍጠርን ዓላማው ያደረገ መድረክ በቴፒ ከተማ እያካሄደ ነው።


 

በመድረኩ ላይ የቢሮው ኃላፊ ዶክተር ኢንጂነር አሥራት ገብረማርያም እንዳሉት የአካባቢ ብክለት ከተፈጥሯዊ ይልቅ በሰው ሰራሽ ምክንያት በስፋት ይከሰታል። 

ለሰው ሰራሽ የአካባቢ ብክለት መስፋት የኅብረተሰቡ የግንዛቤ እጥረት በዋናነት በምክንያትነት እንደሚጠቀስ ገልጸው፣ የህብረተሰቡን ግንዛቤ በትምህርት መቀየር አስፈላጊ በመሆኑ ዛሬ የንቅናቄ ዘመቻ ተጀምሯል ብለዋል።

የአካባቢ መበከል ለአየር ጸባይ ለውጥ መንስኤ ከመሆኑ ባለፈ ለቀጣይ ትውልድ  ፈተና እንደሚሆንም ተናግረዋል።

ለሚቀጥሉት ስድስት ወራት ብክለትን ለመከላከል በንቅናቄ የሚሰራው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ በሁሉም መዋቅሮች በበካይ ቁሶች እና ድርጊቶች አወጋገድ ላይ ትኩረት ይደረጋል ብለዋል።

በክልሉ ጽዱና ለኑሮ ምቹ የሆነ አካባቢን ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት በየደረጃው ያለ አመራርና ኅብረተሰቡ ተግባራዊ ተሳትፎ በማድረግ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።


 

በመድረኩ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የክልሉ መንግስት ረዳት ተጠሪ አቶ በላይ ተሰማ የአየር ንብረት ለውጥ በሰው ህይወት ላይ የሚያስከትለውን ተጽዕኖ በመገንዘብ ብክለትን መከላከል የሁሉም ድርሻ መሆን እንዳለበት ተናግረዋል።

"መንግስት ከሕዝቡ ጋር ተቀናጅቶ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽኖን ለመቋቋም የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነ ነው" ያሉት አቶ በላይ፣ ለእዚህም የአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር ሥራን ለአብነት ጠቅሰዋል።

የአካባቢ መበከል የጤና እክል እንደሚያስከትል ገልጸው፣ "አካባቢን ውብና ለመኖር ምቹ ማድረግ ቱሪዝምን በማሳደግ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ስለሚያረጋገጥ ክልሉ በትኩረት ይሠራል" ብለዋል።

በቴፒ ከተማ እየተካሄደ ባለው ክልላዊ የንቅናቄ መድረክ ላይ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ የዞኖችና የከተማ አስተዳደሮች ባለድርሻ አካላት እየተሳፉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም