በኢንዱስትሪ ፓርኮች ለሚመረቱ ምርቶች በውጭ አገራት ተጨማሪ ገበያ ለማፈላለግ እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በኢንዱስትሪ ፓርኮች ለሚመረቱ ምርቶች በውጭ አገራት ተጨማሪ ገበያ ለማፈላለግ እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 4/2016(ኢዜአ)፦ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ለሚመረቱ ምርቶች በተለያዩ አገራት ተጨማሪ ገበያ ለማፈላለግ ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ገለጸ።
በኮርፖሬሽኑ የኢንቨስትመንት ፕሮሞሽንና ማርኬቲንግ ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዘመን ጁነዲን ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢ ለመፍጠር እየተሰራ ነው።
ጎን ለጎንም በኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚሳተፉ የውጭ ኩባንያዎችን ለመጨመር ከኢንቨስትመንት ኮሚሽንና ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
በተለይም ከአገራት ጋር በሚደረገው ግንኙነት ከኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴርና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በስትራቴጂክ አጋርነት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም ከዚህ ቀደም ከተመሣሣይ አካባቢ የነበረውን የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ፍሰት ለማብዛትና የዓለምን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበ ሌሎች አማራጮችን የማፈላለግ ሥራ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ይህንንም ተከትሎ በተለይም በመካከለኛው ምሥራቅ፣ በአፍሪካ፣ በኤዥያና ደቡብ አሜሪካ ያለውን ግዙፍ ኢንቨስትመንቶች አቅም ወደ ኢትዮጵያ ለመሳብ ትኩረት ማድረጉን ነው ያስረዱት።
“በተጓዳኝም በኢንዱስትሪ ፓርኮች ለሚመረቱ ምርቶች በተለያዩ አገራት ተጨማሪ ገበያ ለማፈላለግና በፓርኮቹ የሚሰሩ ኩባንያዎችን ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
አሁን ላይም ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥርና ሸማች ማኅበረሰብ ያለባቸው እንደ ናይጄሪያና ደቡብ አፍሪካ ያሉ አገሮችን የመግዛት አቅም ጭምር ዳሰሳ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
በመላው ዓለም የሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎችም በኢትዮጵያ ያለውን ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጮችን በማስተዋወቅ ከኮርፖሬሽኑ ጋር በትብብር እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በ2016 አጋማሽ ሪፖርቱ ከ213 ነጥብ 9 ሚሊየን ዶላር በላይ ያስመዘገቡ 23 ባለኃብቶች የሥምምነት ውል ተፈራርመው ሥራ ለመጀመር በሂደት ላይ እንደሚገኙ ገልጿል።
ከ8 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ ተኪ ምርቶችን ለሀገር ውስጥ ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሪ ጫናን መቀነስ መቻሉንና ከ28 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል መፈጠሩንም በሪፖርቱ ገልጿል።