ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አሉ ከሚባሉ የዓለም አየር መንገዶች ጋር ተወዳዳሪ እንዲሆን እየተሰራ ነው - ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 4/2016(ኢዜአ)፦ ለአፍሪካ ኩራት የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አሉ ከሚባሉ የዓለም አየር መንገዶች ጋር ተወዳዳሪ እንዲሆን እየተሰራ ነው ሲሉ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የቦርድ ሰብሳቢ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ተናገሩ።

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር ያለውን ትስስር ይበልጥ ለማጠናከር በያዘው ዕቅድ መሠረት በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ቪዥን 2035 የተሰኙ የመጀመሪያ ዙር የአየር መንገድ የበረራ ሠልጣኞችን በሥነ-ልቦናና በአካል ብቃት አሠልጥኖ አስመርቋል።


 

በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ፤ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ከሌሎች ተቋማት ጋር በትብብር በመስራት ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል።

የአየር መንገድ ራዕይ እንዲሳካ በአገር ፍቅር ስሜት የሚያገለግል የሰው ሀይል በመፍጠር ረገድ ስልጠናው መሰጠቱን ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው በበኩላቸው፤ በአየር ኃይል የተሰጠው ስልጠና ለቀጣይ የበረራ ቴክኒክ ስልጠና አጋዥ መሆኑን አንስተዋል።

አየር መንገዱ በስኬት መቀጠሉ ሁሉም ሰራተኞቹ በፅናት ማገልገል በመቻላቸው ነው ሲሉም ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና አየር ኃይል ታሪካዊ የሆኑ አገራዊ ተቋም እንደመሆናቸው በትብብር ሲሰሩ መቆየታቸውንም ስራ አስፈፃሚው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ከአየር መንገድ የበረራ ዕጩ ሰልጣኞች ባለፈ በደረጃ 7 የሰለጠኑ ነባር ቴክኒሻኖችንም ማስመረቁን ኢቢሲ ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም