ቀጥታ፡

የብሔራዊ ዘላቂ ኢነርጂ ልማት ስትራቴጂ ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 4/2016(ኢዜአ)፦ የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የብሔራዊ ዘላቂ ኢነርጂ ልማት ስትራቴጂን ዛሬ ይፋ አድርጓል።

ስትራቴጂው እንደ አውሮፓውያኑ አቆጠጣር ከ2024 እስከ 2030 ተግባራዊ ይሆናል ተብሏል። 

ስትራቴጂው ይፋ በሆነበት በዚህ መርኃ ግብር ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችን ጨምሮ የአጋር አካላት ተወካዮች ተገኝተዋል።  

የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴርና የተለያዩ ተቋማትን ያቀፈው የባለሙያዎች ቡድን ስትራቴጂውን ለማዘጋጀት 1 ዓመት ከ6 ወር ፈጅቶበታል። 

ከዚህ ቀደም ለስትራቴጂው ስድስት የግብዓት ማሰባሰቢያ አውደ ጥናቶች መካሄዳቸውም ተጠቁሟል።

የጀርመን ዓለም አቀፍ የልማት ትብብር ድርጅት (ጂ አይ ዜድ) ለስትራቴጂው ዝግጅት የፋይናንስና የቴክኒክ ድጋፍ ማድረጉም ተመልክቷል።

የኢነርጂ ተደራሽነትን ማሳደግና ደኅንነት ማረጋገጥ፣ የኢነርጂ አማራጭን ማስፋት፣ የኢነርጂ ብክነትን መቀነስ እንዲሁም ዘላቂነት ያለው የኢነርጂ አስተዳደርን ማጎልበትና በዘርፋ ያለውን አቅም መገንባት የስትራቴጂው ዋነኛ ግቦች ናቸው።

ስትራቴጂው የዘርፉ ተቋማትና ባለ ድርሻ አካላት ያላቸውን ቅንጅት እንደሚያጠናክርና የኢነርጂ አቅምን በአግባቡ መጠቀም ያስችላል ተብሏል።

የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ የፌደራል ተቋማትና የክልል ውኃና ኢነርጂ ቢሮዎች ስትራቴጂውን እንደሚተገብሩት ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎትና የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን ስትራቴጂውን ከሚተግብሩ ተቋማት መካከል ይጠቀሳሉ።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም