የናይጀሪያ ስቶክ ኤክስቼንጅን ጨምሮ ሦስት የውጭ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ሠነደ ሙዓለ ነዋይ ገበያ አባል መሆናቸው ለዘርፉ እድገት ሚናው የጎላ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የናይጀሪያ ስቶክ ኤክስቼንጅን ጨምሮ ሦስት የውጭ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ሠነደ ሙዓለ ነዋይ ገበያ አባል መሆናቸው ለዘርፉ እድገት ሚናው የጎላ ነው
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 4/2016(ኢዜአ)፦የናይጀሪያ ስቶክ ኤክስቼንጅን ጨምሮ ሦስት የውጭ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ሠነደ ሙዓለ ነዋይ ገበያ አባል መሆናቸው ለዘርፉ ቀጣይ እመርታ ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው ተገለጸ።
በመንግሥትና የግል አጋርነት መርህ የተመሰረተው የኢትዮጵያ ሰነድ ሙዓለ ነዋዮች ገበያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶክተር ጥላሁን እስማኤል በድርጅቱ የእስካሁንና ቀጣይ ጉዞ ዙሪያ ለኢዜአ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸውም አንድ ዓመት ከግማሽ ባስቆጠረው እንቅስቃሴ አንዱ የካፒታል ማሰባሰብ ዕቅድ እንደነበር ጠቅሰው፤ ከዕቅዱ ከሁለት እጥፍ በላይ በማሳካት 1 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ካፒታል ተሰባስቧል ብለዋል።
ካፒታል የተሰባሰበው ከ16 ባንኮች፣ ከ12 ኢንሹራንሶችና ከ17 የፋይናንስ ዘርፍ ውጭ ከሆኑ ኩባንያዎች እንደሆኑ ገልጸዋል።
የገበያው ስኬታማ የካፒታል ማሰባሰብ ኩባንያዎች በዘርፉ ያላቸውን ፍላጎትና ንቁ ተሳትፎ የሚያረጋግጥ ጉዳይ በመሆኑ ለቀጣይ ጉዞ ትልቅ አንድምታ እንደሚኖረው አመልክተዋል።
በፋይናንስ ዘርፍ ብቻ 400 ሺህ ገዳማ ባለአክሲዮኖች መኖራቸውን ጠቅሰው የገበያው መቋቋም የተቀላጠፈና ሥርዓት ያለው የፋይናንስ ገበያ ለመዘርጋት አስቻይ ሁኔታ ይፈጥራል ብለዋል።
የሠነደ ሙዓለ ነዋዮች ገበያ ኢትዮጵያውያን በአክሲዮን ገበያ ያላቸውን ተሳትፎ የሚያሳድግ፣ የተራዘመ የፋይናንስ ዕድል የሚፈጥርና ለባንኮች ተጨማሪ ፋይናንስ ፍላጎት የሚጨመር እንደሆነም ገልጸዋል።
በተለይም ከተለመደው የአክሲዮን ገበያ ተጨማሪ አዳዲስ የፋይናንስና ኢንቨስትመንት አገልግሎት የሚያቀላጥፍና አገልግሎታቸውን የሚያዘምን መሆኑን ጠቁመዋል።
የግል 75 በመቶ ከመንግሥት ልማት ድርጅቶች ደግሞ 25 በመቶ ድርሻ ይዞ በተመሰረተው የሠነደ ሙዓለ ነዋዮች ገበያ ከሀገር በቀል ኩባንያዎች ባሻገር ሦስት የውጭ ድርጅቶችን አባል መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
ለአብነትም የረዥም ጊዜ ልምድና ተሞክሮ ያለው የናይጀሪያ ስቶክ ኤክስቼንጅ የሚሰኘው ገበያ ባለድርሻ መሆኑ ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው ነው ብለዋል።
ፋይናንሻል ሴክተር ዲፕኒንግ አፍሪካ' የተሰኘው ለትርፍ ያልተቋቋመ የእንግሊዝ ድርጅትና በአፍሪካ ንግድ ገበያ ልምድ ያለው 'የትሬድና ዴቨሎፕመንት ባንክ' የካፒታል ድርሻ ባለቤት እንደሆኑ ገልጸዋል።
እነዚህ ተቋማት ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸው በተለያዩ ሠነደ ሙዓለ ነዋዮች ገበያ አገልግሎት እንዲሳተፉ ለአብነትም ወደፊት የዕዳ ሰነዶችን እንዲሸጡ በር ከፋች እድል እንደሆነ ነው ያነሱት።
ድርጅቱ ዘመናዊና ደኅንነቱ የተጠበቀና የተቀላጠፈ የሰነደ ሙዓለ ነዋይ ገበያ መመሥረት የሚያስችል ቴክኖሎጂ ገቢራዊ ለማድረግ የግዥና ሌሎች ሂደቶች መጠናቀቃቻውን ገልጸዋል።
የሠነደ ሙዓለ ነዋዮች ገበያ ሕግና መመሪያዎችን ለአብነትም የግጭት አፈታትና ካሳ አከፋፈል የሚደነግጉ ሕገ ደንቦችን የያዙ ጥራዞች ሙሉ በሙሉ ተጠናቀው ለሕዝብ ውይይት ክፍት መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
በተመሳሳይ ቢሮ የማደራጀትና የሰው ኃይል የማሟላትና የሥልጠና ተግባራት በተመሳሳይ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።
የገበያ ልማት ሥራዎች ረገድ ለኩባንያዎችና ግለሰብ ኢንቨስተሮች ግንዛቤ መፍጠርና አቅም ግንባታ ሥራዎች በቀጣይነት ባለው መልኩ ማካሄድ የሚያስችል ዲጂታል አካዳሚ እንደሚከፍት ገልጸዋል።
አካዳሚው የሠነደ ሙዓለ ነዋዮች ገበያን ውጤታማ በሆነ መንገድ በዘላቂነት ለማስኬድ በዲጂታልና በአካል ፕሮግሮሞችን ትምህርትና ሥልጠና የሚሰጥበት እንደሆነ አንስተዋል።
በቀጣይ ዓመት መጀመሪያ ወራት የሠነደ ሙዓለ ነዋዮች ገበያ ግለሰብና ኢንቨስተሮችን ጨምሮ ለገበያው ተዋናይ በይፋ እንደሚጀመርም ዋና ሥራ አስፈጻሚው አረጋግጠዋል።
ይህም አገናኝ አባላትን በማስተዋወቅ ተቋማትና ግለሰቦች ወደ አክሲዮን ገበያው ድርሻ በመግዛት እንደሚቀላቀሉ እንደሚያደርግ ነው ያነሱት።