በ21ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ባህር ዳር ከተማ ከቅዱስ ጊዮርጊስ የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል

728

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 4/2016(ኢዜአ):- በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ21ኛ ሳምንት መርሐ ግብር የሁለተኛ ቀን ውሎ ባህር ዳር ከተማ ከቅዱስ ጊዮርጊስ የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል።

የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ከምሽቱ 1 ሰዓት ላይ በድሬዳዋ ስታዲየም ይደረጋል።

በአሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው የሚመራው ባህር ዳር ከተማ በፕሪሚየር ሊጉ እስካሁን ባደረጋቸው 19 ጨዋታዎች በ9ኙ ሲያሸንፍ 5 ጊዜ ተሸንፎ 5 ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል።

በ19 ጨዋታዎችም 23 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 17 ግቦችን አስተናግዷል።

በሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች በአራቱ ሲያሸንፍ በአንዱ ነጥብ ጥሏል።

አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው በ32 ነጥብ 5ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

የአምናው የሊጉ አሸናፊ ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ በውድድር ዓመቱ ባደረጋቸው 20 ጨዋታዎች 11 ጊዜ ሲያሸንፍ 4 ጊዜ ሽንፈት አስተናግዶ በ5ቱ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል።

በ20ዎቹ ጨዋታዎች 33 ግቦችን ሲያስቆጥር 17 ጎሎች ተቆጥረውበታል።

ክለቡ ካለፉት አምስት የሊጉ ጨዋታዎች በሶስቱ ድል ሲቀናው በአንዱ ሽንፈት በማስተናገድ አንድ ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል።

በአሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ የሚመሩት ፈረሰኞቹ በ38 ነጥብ 3ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

ይህም ዛሬ በሚካሄደው 21ኛ ሳምንት የሊጉ መርሐ ግብር የሁለቱ ክለቦች ፉክክር ተጠባቂ አድርጎታል።

በሊጉ የዛሬ መርሐ ግብር ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ ደግሞ ፋሲል ከነማ ከሀምበሪቾ ዱራሜ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ፋሲል ከነማ ካለፉት አምስት የሊግ ጨዋታዎች በሁለቱ ሲያሸንፍ በአንዱ ተሸንፎ በሁለቱ ደግሞ አቻ ተለያይቷል።

በውበቱ አባተ የሚሰለጥነው ፋሲል ከነማ በ31 ነጥብ 6ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

በአንጻሩ ተጋጣሚው ሀምበሪቾ ዱራሜ ባለፉት አምስት ተከታታይ የሊጉ ጨዋታዎች ሽንፈት አስተናግዷል።

በጊዜያዊ አሰልጣኝ መላኩ ከበደ የሚመራው ሀምበሪቾ በ7 ነጥብ 16ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

በተያያዘ ዜና ትናንት በተደረጉ የ21ኛ ሳምንት የሊጉ ጨዋታዎች ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሃዋሳ ከተማን 2 ለ 1 በማሸነፍ የሊጉን መሪነት ሲያጠናክር ወላይታ ድቻና ድሬዳዋ ከተማ አንድ አቻ ተለያይተዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም