በሐረሪ ክልል የገቢ አሰባሰብን ለማቀላጠፍ በቴክኖሎጂ በመታገዝ የተጀመረው ተግባር ለውጥ እያመጣ ይገኛል - ኢዜአ አማርኛ
በሐረሪ ክልል የገቢ አሰባሰብን ለማቀላጠፍ በቴክኖሎጂ በመታገዝ የተጀመረው ተግባር ለውጥ እያመጣ ይገኛል

ሐረር ፤ ሚያዚያ 4/2016(ኢዜአ)፡- በሐረሪ ክልል የግብር ገቢ አሰባሰብን ለማቀላጠፍ በቴክኖሎጂ በመታገዝ የተጀመረው ተግባር ለውጥ እያመጣ መሆኑን የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ገለጸ።
በቢሮው እየተሻሻለ የመጣው የአገልግሎት አሰጣጥ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተገልጋዮች ተናግረዋል።
የቢሮው ሃላፊ ወይዘሮ ኢክራም አብዱልቃድር ለኢዜአ እንዳሉት፤ ቢሮው በቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራርን በማሳለጥና ህጋዊ አሰራርን በማጎልበት የሚሰበሰበው ገቢ እድገት አሳይቷል።
በተለይ ቢሮው ተገልጋዩ በ"ሲስተም ቴክኖሎጂ "ግብር እንዲከፍል በማመቻቸቱ ገቢው እንዲጨምር አስችሏል ብለዋል።
የተቋም ሪፎርም ተግባራዊ መደረጉና በሰው ሃይል የማደራጀት ስራን ማዘመንም ለውጤቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ገልጸዋል።
እንደ ቢሮ ሃላፊዋ ገለጻ በከተማው 6ቱም ወረዳዎች ላይ ህገ-ወጥ ነጋዴዎችን ወደ ህጋዊነት ለማምጣት ከመጋቢት 3 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ግብረ ሃይል ተሰማርቶ የዘመቻ ስራ እየተከናወነ ይገኛል።
በዘመቻ ስራውም 4ሺህ የሚጠጉ የንግድ ቤቶችን በመመልከት 256 ህገ-ወጥ ነጋዴዎችን ወደ ህጋዊነት ማምጣት መቻሉንና በዚህም እስከ 40 ሚሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን አስረድተዋል።
ክልሉም በተያዘው የበጀት ዓመት ስምንት 8 ወራት ከቀጥተኛና ቀጥተኛ ካልሆነ ታክስ፣ ታክስ ካልሆነና ከማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ከ1 ቢሊየን 330 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ መቻሉን ተናግረዋል።
የተሰበሰበው ገቢም ከእቅዱ 98 በመቶ እንዲሁም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ደግሞ 24 በመቶ ብልጫ እንዳለው አመልክተዋል።
በክልሉ የሚሰበሰበውን ገቢ ከማጎልበት አንጻር የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ወይዘሮ ኢክራም ገልጸዋል።
ከክልሉ ግብር ከፋዮች መካከል አቶ ተስፋለኔ ገለታ በሰጡት አስተያየት፤ የገቢው ሰብሳቢ መስሪያ ቤት እየሰጣቸው ያለው አገልግሎት እየተሻሻለ ከዚህ ቀደም ይታዩ የነበሩ እንግልቶችን እያስቀረ መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይ በከተማው ጎዳና ላይ የተስፋፋውን ህገ-ወጥ ንግድ ወደ ህጋዊነት ለማምጣት እየተከናወነ የሚገኘው ስራም መጠናከር አለበት ሲሉ ገልጸዋል።
ሌላኛው ግብር ከፋይ አቶ ተክለብርሃን ተክለጨርቆስ በበኩላቸው፤ የቢሮው ሰራተኞች ለተገልጋዩ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት እያከናወኑ የሚገኘው ስራ አበረታች ቢሆንም አሁንም ከሰዓት አጠቃቀም ጋር የሚታዩ ውስንነቶች መስተካከል እንዳለባቸው ጠቁመዋል።
ግብር ለመክፈል በተደጋጋሚ ጊዜ ወደ ቢሮው እንደሚመጡ የተናገሩት ሌላው ግብር ከፋይ አቶ ገዛኸኝ ስዩም፤ በተለይ በአሁኑ ወቅት የተቀላጠፈ አገልግሎት እያገኙ መሆኑን አመልክተዋል።
በቴክኖሎጂ በመታገዝ የተጀመረው አሰራርም ጊዜንና ጉልበትን እንደቆጠበላቸው ተናግረዋል።
በሐረሪ ክልል 29ሺህ የሚሆኑ ግብር ከፋዮች እንደሚገኙ ከገቢዎች ቢሮው የተገኘ መረጃ ያመላክታል።