በሳዑዲ አረቢያ በማቆያ ጣቢያ የሚገኙ ዜጎችን የመመለሱ ሥራ ነገ ይጀመራል - ኢዜአ አማርኛ
በሳዑዲ አረቢያ በማቆያ ጣቢያ የሚገኙ ዜጎችን የመመለሱ ሥራ ነገ ይጀመራል
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 03/2016 (ኢዜአ):- በሳዑዲ አረቢያ በማቆያ ጣቢያ የሚገኙ ዜጎችን በተቀናጀ መንገድ የመመለሱ ሥራ ነገ እንደሚጀመር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ገለጹ።
በሚኒስትር ዴኤታዋ የተመራው የመንግሥት ልዑክ ቡድን በሳዑዲ አረቢያ ሪያድ የኢትዮጵያ ኤምባሲ እና የጂዳ ቆንስላ ጀነራል ሰራተኞች እና የኮሙኒቲ አስተባባሪዎች ጋር በመወያየት በተመላሾች መለየት እና መመለስ ላይ የስራ አቅጣጫ ሰጥቷል።
አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ዜጎችን ወደ ሀገራቸው የመመለስ ስራው ዜጋ ተኮር የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ተግባራዊነትን ያረጋገጠ ነው ብለዋል።
በሚኒስትር ዴኤታዋ ሪያድ እና ጂዳ አካባቢ በማቆያ ጣቢያ የሚገኙ ኢትዮጵያውንን ወደ ሀገር ቤት የመመለሱ ስራ ነገ ሚያዚያ 04 ቀን 2016ዓ.ም እንደሚጀመር አቅጣጫ ተቀምጦ ዝግጅቱ መጠናቀቁን አብራርተዋል።
የልዑካን ቡድኑ ከጅዳ አስተዳደሮች ጋር ውይይት በማድረግ በሽመሲ ማቆያ ጣቢያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን መመልከታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።