ብሪታንያ የኢትዮጵያ አበባ ከግብር ነጻ ወደ ሀገሯ እንዲገባ መፍቀዷ የዘርፉን የወጪ ንግድ የሚያሳድግ ነው - የኢትዮጵያ አበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ አምራች ላኪዎች ማህበር - ኢዜአ አማርኛ
ብሪታንያ የኢትዮጵያ አበባ ከግብር ነጻ ወደ ሀገሯ እንዲገባ መፍቀዷ የዘርፉን የወጪ ንግድ የሚያሳድግ ነው - የኢትዮጵያ አበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ አምራች ላኪዎች ማህበር
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 3/2016(ኢዜአ)፦ ብሪታንያ የኢትዮጵያ አበባ ከግብር ነጻ ወደ ሀገሯ እንዲገባ መፍቀዷ የዘርፉን ወጪ ንግድ የሚያሳድግ መሆኑን የኢትዮጵያ አበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ አምራች ላኪዎች ማህበር ገለፀ።
የብሪታንያ ንግድ ኮሚሽን ባወጣው መግለጫ ብሪታንያ የአበባ ምርቶችን ወደ ሀገሯ በሚያስገቡ ነጋዴዎች ላይ ጥላው የነበረውን ግብር አንስታለች፡፡
ከዚህ በፊት የአበባ ምርቶች ወደ ብሪታንያ ሲገቡ ስምንት በመቶ ግብር ይከፈልባቸው እንደነበርና ይህም ከዛሬ ሚያዚያ 3 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ለሁለት ዓመት መነሳቱን ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡
ግብር ከተነሳላቸው ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ እንደምትገኝበት በመግለጫው ተጠቅሷል።
ይህን በማስመልከት ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የኢትዮጵያ አበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ አምራች ላኪዎች ማህበር ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ዘውዴ እንደተናገሩት ብሪታንያ የኢትዮጵያ አበባ ያለ ግብር ወደ ሀገሯ እንዲገባ መፍቀዷ በኢትዮጵያ ያሉ አበባ አምራቾችን የወጪ ንግድ የሚያሳድግ ነው።
የግብር ክፍያው መነሳት በኢትዮጰያ ያሉ አበባ አምራቾች ምርቶቻቸውን ለተጠቃሚዎች በማቅረብ የበለጠ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ያስችላቸዋል ሲሉም ገልፀዋል።
የግብር ክፍያው መነሳት ትልቅ እድል ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ በቀጣይ በቅንጅት በመስራት ያገኘነውን ዕድል በአግባቡ ልንጠቀምበት ይገባል ብለዋል።
በዘርፉ ያለውን ኢንቨስትመንት የበለጠ ለማሳደግ የመሬት አቅርቦትንና የድጋፍ ስርዓቱን ማሻሻል ይገባል ሲሉ አቶ ቴዎድሮስ ተናግረዋል።
ብሪታንያ ወደ ሀገሯ ለሚገቡ የአበባ ምርቶች ይፋ ያደረገችው የግብር እፎይታ ለሁለት ዓመት እንደሚቆይና ይህም ያልተገደበ መጠን ያላቸው አበቦች ወደ ብሪታንያ እንዲገቡ የሚያስችል እንደሆነ በመግለጫው ተመላክቷል።