ማህበሩ በአማራ ክልል ለድንገተኛ አደጋዎች ምላሽ የሚውል የ100 ሚሊዮን ብር ፕሮጀክት ሥራ አስጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
ማህበሩ በአማራ ክልል ለድንገተኛ አደጋዎች ምላሽ የሚውል የ100 ሚሊዮን ብር ፕሮጀክት ሥራ አስጀመረ
ደሴ፤ ሚያዝያ 3/2016 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በአማራ ክልል ደቡብና ሰሜን ወሎ ዞኖች የተቸገሩ ወገኖችን በቀጥታ ድጋፍና በመልሶ ማቋቋም ለማገዝ የሚያስችል የ100 ሚሊዮን ብር ፕሮጀክት ሥራ ማስጀመሩን አስታወቀ።
ማህበሩ የፕሮጀክቱን ይፋዊ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ዛሬ በደሴ ከተማ አካሂዷል።
በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ዘራ ታደሰ እንደገለጹት፤ ማህበሩ በሰው ሠራሽና በተፈጥሮ አደጋ ለችግር የሚጋለጡ ወገኖችን በማገዝ የድርሻውን እየተወጣ ይገኛል።
በዚህም በአካባቢው በነበረ የሰሜኑ ጦርነት፣ በድርቅና ሌሎችም ድንገተኛ አደጋዎች ለችግር የተዳረጉ ወገኖችን ለማገዝ የ100 ሚሊዮን ብር ፕሮጀክት ወደ ሥራ ማስገባቱን ገልጸዋል።
ፕሮጀክቱ በቀጣይ አንድ ዓመት ተኩል ቆይታው 46ሺህ የሚጠጉ ዜጎችን በቀጥታ የገንዘብ ድጋፍ፣ በንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ በእንስሳት እርባታ እና በሌሎች የገቢ ማስገኛ ሥራዎች ተጠቃሚ ያደርጋል።
እንዲሁም የክህሎት ማበልጸጊያና የግንዛቤ ፈጠራ ስልጠና በመስጠት፣ በአምቡላስ እንዲሁም በግብዓት አቅርቦት ድጋፍ ያደርጋል።
በመሆኑም ፕሮጀክቱ ውጤታማ እንዲሆን የዞኑ አመራሮችና ህብረተሰቡ አስፈላጊውን ትብብር በማድረግ የድርሻቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።
በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ኃላፊ አቶ ሻምበል ዋለ በበኩላቸው፤ በአካባቢው በነበረ የሰሜኑ ጦርነት፣ በድርቅና ሌሎችም አደጋዎች ለችግር የተጋለጡ ዜጎችን ለመደገፍ እየተሰራ ነው።
በዚህም በማህበሩ "መሰላል" የተሰኘ ፕሮጀክት በዞኖቹ ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን በመለየትና ሌሎች ቅድመ ዝግጅቶችን በማጠናቀቅ ወደሥራ መገባቱን ገልጸዋል።
ለፕሮጀክቱ ስኬታማነት አስተዳደሩ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል በማድረግ የድርሻውን ይውጣል ያሉት ደግሞ የደቡብ ወሎ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ አሊ ይማም ናቸው።
ፕሮጀክቱ በዞኑ መተግበሩ ተፈናቃይ ወገኖችን ከማገዝ ባለፈ ሌሎች የተቸገሩ ወገኖችን ለመደገፍና መልሶ ለመቋቋም ከፍተኛ እገዛ እንደሚኖረው ተናግረዋል።
የሰሜን ወሎ ዞን አስተዳደር ተወካይ አቶ ጥሪቴ በላይ በበኩላቸው፤ ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው በዞኑ የተጠለሉ ወገኖችን ጨምሮ በተለያየ ምክንያት ለችግር የተዳረጉ ዜጎች ይገኛሉ።
በተለይ ሴቶችና ህጻናቶች በልዩ ሁኔታ ድጋፍ እንደሚፈልጉ ጠቁመው፤ ለዚህም የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ያስጀመረው ፕሮጀክት ችግሩን ያግዝል ብለዋል።
በፕሮጀክቱ ማስጀመሪያ ስነ ስርዓት ለይ አመራሮችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላትም ተሳታፊ ሆነዋል።