ሁለተኛው አለም አቀፍ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ በአዲስ አበባ ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
ሁለተኛው አለም አቀፍ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ በአዲስ አበባ ይካሄዳል
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 3/2016(ኢዜአ)፦ሁለተኛው አለም አቀፍ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ አስታወቀ።
ጉባዔው በመጪው ሰኞ በአዲስ አበባ መካሄድ ይጀምራል።
የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ በሰጠው መግለጫ በመርኃ ግብሩ ፣ ከተለያዩ አገራት የሚመጡ የሃይማኖት አባቶች ፣የተለያዩ አደረጃጀቶች ፣የዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡና የዘርፉ ተመራማሪዎች እንደሚታደሙበት ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ጠቅላይ ፀሃፊ ቀሲሳ ታጋይ ታደለ እንዳስታወቁት ፣ ኮንፈረንሱ በአለም አቀፍ ደረጃ ሁለንተናዊ ትብብርን በሚያጠናክርና በሰላም ግንባታ እንዲሁም በአለም አቀፋዊና አህጉራዊ ጉዳይች ላይ ይመክራል ።
ከጉባዔው ጎን ለጎን የኢትዮጵያን ምድረ-ቀደምትነት የሚያሳዩ የተለያዩ የጉብኝት መርኃ ግብሮች መዘጋጀታቸውንም አንስተዋል።
በተለይም በሃይማኖት መቻቻልና በአረንጓዴ ልማት ስራዎች የተገኙ ውጤቶችን ይቀርቡበታል ብለዋል፡፡
የጉባዔው ታዳሚዎች የአዲስ አበባን የአፍሪካ ህብረት መዲናነት የሚያረጋግጡ የልማት ስራዎችን እንዲጎበኙ ፕሮግራም መያዙን አንስተዋል።
በጉባዔው ውይይት የሚደረግባቸው ጉዳዮች ለአፍሪካ ህብረትና ለቡድን 20 አባል አገራት እንደሚቀርቡ ተናግረዋል።
ጉባዔው በመጪው ሰኞና ማክሰኞ በአፍሪካ ህብረት የሚካሄድ ሲሆን ከ37 የበለጡ አገራት ይሳተፋበታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡