የዓለም የሥነ-ጥበብና የኢትዮጵያ የጃዝ ቀን በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ይከበራል - ኢዜአ አማርኛ
የዓለም የሥነ-ጥበብና የኢትዮጵያ የጃዝ ቀን በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ይከበራል
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 3/2016(ኢዜአ)፦የዓለም ሥነ-ጥበብና የኢትዮጵያ የጃዝ ቀን ሚያዝያ 5 እና 6/2016 ቀን በኢትዮጵያ ሣይንስ አካዳሚ ለመጀመሪያ ጊዜ በአውደ ርዕይና በጃዝ ኮንሰርት ሊከበር ነው።
የዓለም የሥነ-ጥበብና የኢትዮጵያ የጃዝ ቀንን አስመልክተው የኢትዮጵያ ሣይንስ አካዳሚና የአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያ ሣይንስ አካዳሚ ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ተከተል ዮሐንስ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ የዓለም የሥነ-ጥበብና የኢትዮጵያ ጃዝ ሙዚቃ ቀን ፌስቲቫል ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ይካሄዳል።
በመርኃ ግብሩም በአካዳሚው በብላቴን ጌታ ኅሩይ የሥነ-ጥበባት ማዕከል እንደሚካሄድ ገልጸዋል።
በዝግጅቱም የሥዕል አውደ ርዕይ፣ ግጥም ባጃዝና የጃዝ ሙዚቃ ኮንሰርት እንደሚካሄድ ጠቁመው በተለይም የታላላቅ ሠዓሊያን ሥራዎች የሚቀርቡበት አውደ ርዕይ ለአንድ ሣምንት እንደሚቆይ ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ ሰርጸ ፍሬስብሐት በበኩላቸው በመርኃ ግብሩ የጃዝ ሙዚቃ ተጫዋችና አቀናባሪ ሳሙኤል ይርጋ የጃዝ ኮንሰርት ይቀርባል ብለዋል።
በጃዝ ኮንሰርቱ ላይ የያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤትና የመካነየሱስ ሴሚናርየም የጃዝ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የመድረክ ሥራዎቻቸውን እንደሚያቀርቡም አመልክተዋል።
ከዓለም የሥነ-ጥበብ ማሰልጠኛ ተቋም ጋር በመተባበርም ከቅዳሜ ጀምሮ ሕፃናት በቀለም ቅብ ራሳቸውን የሚገልጹበት ዝግጅትም እንደሚካሄድም አቶ ሰርጸ ተናግረዋል።
የዓለም የሥነ-ጥበብ ቀን ኤፕሪል 15 ሆኖ እንዲከበር የተወሰነው በ2019 ዓ.ም በተካሄደው በ40ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጉባዔ ላይ ነው።
ዕለቱ የተመረጠው ታላቁ የሥነ-ጥበብ ሰው ለዮናርዶ ዳ ቬንቺ የተወለደበት ቀን ስለሆነ ነው።
የዓለም ሥነ-ጥበብ ቀን ከአለ ፈለገ ሰላም የሥነ-ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለም ለስድስተኛ ጊዜ እንደሚከበር ገልጸዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) ኤፕሪል 30 የዓለም ጃዝ ቀን ሆኖ እንዲከበር እንደ አውሮፓውያኑ አቆጠጣር በ2011 ወስኗል።