የሰብዓዊ ድጋፍ ስራዎችን ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የማስፋት ፍላጎት አለኝ- የዓለም የምግብ ፕሮግራም - ኢዜአ አማርኛ
የሰብዓዊ ድጋፍ ስራዎችን ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የማስፋት ፍላጎት አለኝ- የዓለም የምግብ ፕሮግራም
አሶሳ ፤ ሚያዚያ 3/2016(ኢዜአ)፦ የአለም ምግብ ፕሮግራም (WFP) በተለያዩ ክልሎች የሚያደርገውን ሰብዓዊ ድጋፍ ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልም የማስፋት ፍላጎት እንዳለው አስታወቀ።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን በክልሉ አሁን ያለው ሰላም ሁሉንም ዓይነት የልማት ስራ ለማከናወን ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ገልጸዋል።
የዓለም የምግብ ፕሮግራም ልዑካን ቡድን ከክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን ጋር ዛሬ በአሶሳ ከተማ ተወያይቷል።
በውይይቱ ወቅትም የአለም ምግብ ፕሮግራም የምስራቅ አፍሪካ እና የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ክሪስ ኒኮይ እንደገለፁት፤ የዓለም የምግብ ፕሮግራም በጋምቤላ፣ በሶማሌ እና በሌሎች ክልሎች የሰብአዊ ድጋፍ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል።
በክልሎቹ እየተከናወኑ ከሚገኙ ተግባራት መካከል የህብረተሰቡን ህይወት የሚቀይሩ ሰብዓዊ እገዛዎችን ጨምሮ በጤናው ዘርፍ በተለይም የእናቶች እና ህጻናት ጤናን የሚያሻሽሉ ስራዎች እንደሚገኙበት ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
እነዚህን ተሞክሮዎች መሠረት በማድረግም የዓለም የምግብ ፕሮግራም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ የሚካሄዱ የመልሶ ማቋቋም ስራዎችን እንደሚደግፍ ዳይሬክተሩ አመልክተዋል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን በበኩላቸው በክልሉ አሁን ያለው ሰላም ሁሉንም ዓይነት የልማት ስራ ለማከናወን የፈጠረውን ምቹ ሁኔታ አስመልክተው ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ ተፈናቃይ ወገኖችን በዘላቂነት መልሶ ለማቋቋም የተጀመሩ ስራዎችን እንዲሁም የባለድርሻ አካላትን እገዛ የሚሹ ጉዳዮችን የተመለከተ ገለጻም አድርገዋል።