ኢትዮጵያ በቻይና የግሎባል ፐብሊክ ሴኩሪቲ ትብብር ፎረም ዳይሬክተሮች ቦርድ ስብሰባ ላይ እየተሳተፈች ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በቻይና የግሎባል ፐብሊክ ሴኩሪቲ ትብብር ፎረም ዳይሬክተሮች ቦርድ ስብሰባ ላይ እየተሳተፈች ነው
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 3/2016 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በቻይና ናንቶንግ ከተማ እየተካሄደ በሚገኘው የግሎባል ፐብሊክ ሴኩሪቲ ትብብር ፎረም ዳይሬክተሮች ቦርድ ስብሰባ ላይ እየተሳተፈች ትገኛለች።
የግሎባል ፐብሊክ ሴኩሪቲ ትብብር ፎረም የዳይሬክተሮች ቦርድ አባል የሆኑት የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል ከሚያዚያ 1 እስከ 3/2016 ዓ.ም እየተካሄደ ባለው በስብሰባ ላይ እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡
በመድረኩ የፎረሙ ዓመታዊ የስራ ክንውን ሪፖርት በተመለከተ፣ የግሎባል ሴኩሪቲ ኢንዴክስ ላይ ስለሚደረገው ጥናት ሂደት እና የፎረሙ የ2024 ዓመታዊ ኮንፈረስ ዝግጅትን አስመልክቶ ውይይት በማድረግ የተለያየ ውሳኔዎችን ያሳልፋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የትብብር ፎረሙ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከዘጠኝ ሀገራት የተውጣጡ ከፍተኛ የቦርድ ዳይሬክተሮች የሚመራ መሆኑንና በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የህዝብ ደኅንነት ላይ በማተኮር የሀገሮችን የሕግ አስከባሪ ተቋማትን በማስተባበር ልዩ ልዩ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ተመላክቷል፡፡
ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ከቦርድ አመራር ጉባኤው ጎን ለጎን በቻይና የሚገኙ ልዩ ልዩ ተቋማትን መጎብኘታቸው የተገልጿል፡፡
በዚህም በጃንሱ ግዛት የሚገኘው ሞተር ሳይክል አምራች የሆነውን ሲ ኤፍ ሞተር መጎብኘታቸው የተጠቀሰ ሲሆን፤ ካምፓኒው በኢትዮጵያ ቅርንጫፉን በመክፈት ለመስራት ፍላጎት እንዳለው መግለጹ ተጠቁሟል፡፡
ኮሚሽነር ጀነራሉ በተጨማሪም የቺንጃን ፖሊስ ኮሌጅን መጎብኘታቸውንና፤ በአሁኑ ወቅት በኮሌጁ ነጻ የትምህርት እድል አግኝተው እየሰለጠኑ ላሉት የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አባላት ኮሌጁ ለሰጠው ነፃ የትምህርት ዕድል ማመስገናቸው ተገልጿል፡፡
በኢትዮጵያ ፖሊስ ዩንቨርሰቲ የኢንተርናሽናል ፖሊስ ሊደርሺፕ ኢንስቲትዩት ለማቋቋም እየተሰራ መሆኑን የጠቀሱት ኮሚሽነር ጀነራሉ፤ ኮሌጁ ከዩንቨርስቲው ጋር በትብብር እንዲሰራ መጠየቃቸውን ከፌዴራል ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።