የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ21ኛ ሳምንት መርኃ ግብር ዛሬ ይጀመራል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ21ኛ ሳምንት መርኃ ግብር ዛሬ ይጀመራል
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 3/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ21ኛ ሳምንት መርኃ ግብር ዛሬ በሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎች በድሬዳዋ ስታዲየም ይጀመራል።
በሳምንቱ የመክፈቻ ጨዋታ የሊጉ መሪ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሃዋሳ ከተማ ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በፕሪሚየር ሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ የሊጉ ጨዋታዎች በሁለቱ ድል ሲቀናው በአንዱ ተሸንፏል። ሁለት ጊዜ አቻ ወጥቷል።
ተጋጣሚው ሃዋሳ ከተማ በበኩሉ ካለፉት አምስት ጨዋታዎች በሁለቱ ሲያሸንፍ በሁለቱ ሽንፈት አጋጥሞታል። አንድ ጊዜ ነጥብ ተጋርቷል።
ክለቡ በ26 ነጥብ 10ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ወላይታ ድቻ ከድሬዳዋ ከተማ ከምሽቱ 1 ሰዓት ላይ የሚያደርጉት ጨዋታ ሌላኛው የ21ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ነው።
በአሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ የሚመራው ወላይታ ድቻ በሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ጨዋታዎች ድል አልቀናውም። በሶስቱ ሲሸነፍ ሁለት ጊዜ አቻ ወጥቷል።
ወላይታ ድቻ በ24 ነጥብ 12ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ተጋጣሚው ድሬዳዋ ከተማ ካለፉት አምስት የሊግ ጨዋታዎች በሶስቱ ድል ያስመዘገበ ሲሆን አንድ ጊዜ አቻ ሲወጣ አንድ ጊዜ ደግሞ ሽንፈት ገጥሞታል።
በአሰልጣኝ ኮማንደር ሽመልስ አበበ የሚመራው ድሬዳዋ ከተማ በ29 ነጥብ 9ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ21ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ነገም ቀጥሎ ሲውል ፋሲል ከነማ ከሀምበሪቾ ዱራሜ ከቀኑ 10 ሰዓት፤ ባህር ዳር ከተማ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ከምሽቱ 1 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
የ21ኛ ሳምንት ጨዋታዎች እስከ ሚያዚያ 6 ቀን 2016 ዓ.ም ይቆያሉ።
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነትን የሃዋሳ ከተማው አጥቂ አሊ ሱሌይማን በ11 ግቦች ይመራል። ዩጋንዳዊው የድሬዳዋ ከተማ ተጫዋች ቻርልስ ሙሲጌ በ9 ግቦች ይከተላል።