በመቀሌ ከተማ ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ ማህበራት የሚሳተፋበት ኤግዚቢሽንና ባዛር ሊዘጋጅ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በመቀሌ ከተማ ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ ማህበራት የሚሳተፋበት ኤግዚቢሽንና ባዛር ሊዘጋጅ ነው
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 1/2016(ኢዜአ)፦ በመቀሌ ከተማ ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ የህብረት ስራ ማህበራት የሚሳተፋበት አገር አቀፍ ኤግዚቢሽንና ባዛር ሊዘጋጅ መሆኑን የኢትዮጵያ ህብረት ስራ ኮሚሽን አስታወቀ።
ኤግዚቢሽንና ባዛሩ ከሚያዚያ 12 እስከ 19 ቀን 2016 ዓ.ም ''ህብረት ባዛር እና ኤግዚቢሽን'' በሚል መሪ ሀሳብ እንደሚካሄድ ተገልጿል።
ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ የህብረት ስራ ማህበራት የሚሳተፉበት ሀገር አቀፍ ባዛርና ኤግዚቢሽን እንዲሁም ሲምፖዚየም መሆኑም ተጠቁሟል።
ኤግዚቢሽኑን በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የህብረት ስራ ማህበር እና የገበያ ልማት ኤጀንሲ ከኢትዮጵያ ህብረት ስራ ኮሚሽን ጋር በመተባበር እንደሚያዘጋጁት ከተቋሙ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
የኢትዮጵያ ህብረት ስራ ኮሚሽን በመቀለ ከተማ ለሚካሄደው ኤግዚቢሽንና ባዛር ክልሎችን የማስተባበር ስራ እየሰራ መሆኑን ጠቁሟል።
በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የህብረት ስራ ማህበር እና ገበያ ልማት ኤጀንሲ ኃላፊ አቶ ነጋ ሰፋ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ኤግዚቢሽንና ባዛሩ ከክልሎች ጋር ያለውን የገበያ ትስስር ማጠናከርን ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
በተጨማሪም ምርቶችን በቀጥታ ለሸማቾች በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ገበያን በማረጋጋትና የኑሮ ውድነትን ለማቃለል የሚደረገውን ጥረት ለመደገፍና ለማስፋት ያለመ መሆኑን ጠቁመዋል።
በተለያዩ ክልሎች ያሉ ማህበራት ምርቶቻቸውን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያቀርቡ ለማድረግ የቅድመ ዝግጅት ስራው እየተከናወነ መሆኑን አብራርተዋል።
በኤግዚቢሽንና ባዘሩ ከሁለት መቶ በላይ የህብረት ስራ ማህበራት እንደሚሳተፉ የገለጹት ኃላፊው የተለያዩ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶች እንደሚቀርቡም ገልጸዋል።
ኤግዚቢሽንና ባዛሩ ለተከታታይ ስምንት ቀናት እንደሚቆይ ገልጸዋል።