ቀጥታ፡

በሳዑዲ አረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን የመመለስ ስራ በቅርቡ ይጀመራል - የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር 

 አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 1/2016(ኢዜአ)፦ በሳዑዲ አረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ 70 ሺህ የሚጠጉ ዜጎችን የመመለስ ስራ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚጀመር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ነብዩ ተድላ መንግስት በውጭ ጉዳይ ፖሊሲው ትኩረት ሰጥቶ እየሰራበት ከሚገኝበት ጉዳይ አንዱ በተለያዩ አገራት በአስቸጋሪ ሁኔታ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ወደ አገር ቤት የመመለስና ማቋቋም እንደሆነ ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ አኳያም በሶስተኛው ምዕራፍ ሳዑዲ አረቢያ 70 ሺህ የሚጠጉ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸውን ኢትዮጵያውያንን በዘመቻ መልክ ለመመለስ ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤  ለዚህም በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ የሚመራና ከ16 ተቋማት የተወጣጣ ብሔራዊ ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱን ጠቁመዋል።

በአምባሳደር ብርቱካን አያኖ የተመራና የከፍተኛ መንግስት አመራሮችን ያቀፈ ልዑካን ቡድን በሳዑዲ አረቢያ እንደሚገኝና ዜጎችን ለመመለስ የሚያስችሉ አጋዥ ስምምነቶችን መፈራረሙን ነው ያመለከቱት።

ልዑካን ቡድኑ ከሳዑዲ አረቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ኢሚግሬሽን፣ደህንነትና የስደት ጉዳዮች ተቋማት ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር በጉዳዩ ላይ ምክክር ማድረጉን አመልክተዋል።

ቡድኑ ሪያድና ጅዳ ከሚገኙት የኢትዮጵያ ሚሲዮኖች ጋር በመሆን በእስር ቤቶችና በተለያዩ ማቆያዎች የሚገኙ ዜጎችን ኢትዮጵያዊነት የማረጋገጥ፣ የመመዝገብና ለጉዞ ዝግጁ የማድረግ ስራዎችን እንደሚያከናውን ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያውያኑን ወደ አገር ቤት በመመለስ ስራው ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ዜጎችን የመለየት፣ ሙሉ ጤንነታቸውን የማረጋገጥና ሎጅስቲክስ የማሟላት ስራ እንደሚከናወን የገለጹት አቶ ነብዩ፤  በዚህም ሴቶች፣ሕጻናት፣እናቶች፣ነፍሰ ጡሮች፣እድሜያቸው የገፉና የጤና ችግር ያለባቸው ግለሰቦች  ቅድሚያ እንደሚሰጣቸው አመልክተዋል።

ከዚህ ቀደም ዜጎችን የመመለስ ስራ በመደበኛ የንግድ በረራ በሳምንት ሶስት ቀናት እንደሚከናወን አስታውሰው በአሁኑ ዙር ከሳዑዲ አረቢያ የሚመጡት ኢትዮጵያውያን ቁጥር ከፍተኛ ከመሆኑ አንጻር በተለመደው የበረራ አገልግሎት በአጭር ጊዜ ለመመለስ አስቸጋሪ እንደሚሆን አንስተዋል።

ይህንንም ከግምት ውስጥ በማስገባት በቀን አራት ጊዜ በሳምንት 12 በረራዎችን በማድረግ ዜጎች በፈጣንና አጭር ጊዜ ውስጥ ለመመለስ እቅድ መያዙን ነው ቃል አቀባዩ ያመለከቱት። 

ዜጎች ወደ አገር ከተመለሱ በኋላ ወደ የሚኖሩበት ቦታ የመመለስ ተግባር ከፌደራል ተቋማት ባለፈ ክልሎች የራሳቸውን ዝግጅት እያደረጉ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ለዜጎች መጠለያ የመስራት እንዲሁም ከዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት(አይኦኤም) እና ሌሎች አጋር አካላት ጋር በመሆን የመልሶ ማቋቋም ስራ እንደሚያከናውን አብራርተዋል።

የከፍተኛ መንግስት አመራሮች ያቀፈው የልዑካን ቡድን በሳዑዲ አረቢያ ያለውን ስራ አጠናቆ ከተመለሰ በኋላ ዜጎቹን የመመለስ ተግባር በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚጀመር ነው አቶ ነብዩ የጠቆሙት።

በ2015 ዓ.ም 136 ሺህ የሚሆኑ ዜጎች ከሳዑዲ አረቢያ መመለሳቸውን አስታውሰዋል።

በተያያዘም በ2016 ዓ.ም በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ስራ 50 ሺህ 327 ዜጎች ወደ አገራቸው መመለሳቸውን ጠቁመዋል።

29 ሺህ 872 ዜጎች ከመካከለኛው ምስራቅ መመለሳቸውንና ከነዚህም ውስጥ ከ21 ሺህ በላይ ዜጎች የሚሆኑት ከሳዑዲ አረቢያ እንደሆኑም ጠቁመዋል።

ከ20 ሺህ በላይ ዜጎች ከአፍሪካ አገራት መመለሳቸውንም በመግለጽ።

መንግስት ዜጎች ክብራቸውንና መብታቸው ተጠብቆ ሕጋዊ የስራ ስምሪት እንዲከተሉ ለማድረግ እየሰራ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ እስከ አሁን  ባለው ሂደት ከሳዑዲ አረቢያ፣ሊባኖስ፣ዮርዳኖስና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ጋር ሕጋዊ የስራ ስምሪት ስምምነት መፈጸሙን አመልክተዋል።

ከኩዌት፣ኦማንና ባህሬን ጋር የስራ ስምሪት ስምምነት ለመፈራረም ድርድር በመካሄድ ላይ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም