ታላቁ የረመዳን ወር - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ የረመዳን ወር
ታላቁ የረመዳን ወር
‹‹ረመዳን›› የአረብኛ ቃል ሲሆን በሂጅራ አቆጣጠር የዘጠነኛው ወር ስም መጠሪያ ነው። የረመዳን ወር ቅዱስ ቁርኣን ለሰው ልጆች ሁሉ ይደርስ ዘንድ ለነብዩ መሀመድ መውረድ የጀመረበት በመሆኑ ምንዳዋ ከሺሕ ወር በላይ እንደሆነ ይታመናል።
‹‹ጾም›› የሚለው ቃል በእስልምና ‹‹ማቆም›› ወይም ‹‹መከልከል›› የሚል ፍች አለው። በሸሪኣዊ አገባቡ ደግሞ ለአላህ ትእዛዝ ለመገዛት በሚል ውስጣዊ ውሳኔ ከፈጅር እስከ ጸሐይ ግባት ከምግብ፣ ከመጠጥና እኩይ ቃል ከመናገርና እኩይ ድርጊት ከመፈጸም መታቀብ፣ ወዘተ የሚል ጥቅል ትርጉም እንዳለው መሐመድ-ዓሊ (ዶ/ር) ጾምና የጾም ፍች ማህበረ ባህላዊ ፋይዳ በእስልምና በሚል ባዘጋጁት ጽሁፍ አስፍረዋል።
በእስልምና ጾም በመደበኛ ጾምና በሱና ጾም ይከፈላል። የሱና ጾም በልዩ ልዩ ምክንያቶችና ሁኔታዎች አብዛኛውን ጊዜ በግል የሚፈጸም ግዴታ የሌለበት የጾም አይነት ሲሆን፤ የሱና ጾም በማንኛውም ጊዜ ሊጾም ይቻላል። መደበኛው ጾም ደግሞ በጊዜ ገደብ ውስጥ በቡድን የሚጾም ግዴታ የሆነ የጾም አይነት ነው። ይህ የግዴታ ወይም መደበኛ ጾም በሂጅራ አቆጣጠር ዘጠነኛ በሆነው የረመዳን ወር ይጾማል።
የሂጅራ የጊዜ አቆጣጠር በጨረቃ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ የረመዳን ወር ሀያ ዘጠኝ ወይም ሰላሳ ቀን ስለሚሆን የጾሙም ጊዜ ሀያ ዘጠኝ ወይም ሰላሳ ቀን ይሆናል። የረመዳን ወር ጾም ከእስልምና አምስቱ ማዕዘናት አንደኛው ነው።
የረመዳን ወር ጾም እድሜው ለደረሰና ጤነኛ ለሆነ ሙስሊም ሁሉ ግዴታ በመሆኑ በልዩ ልዩ አሳማኝ ምክንያቶች ለምሳሌ በበሽታና በጉዞ፣ በእርግዝናና ልጅ በማጥባት ምክንያት በወሩ ለመጾም ያልቻለ ሰው የታመመው ከበሽታው ሲድን፣ ተጓዡም ከጉዞው ሲመለስ፣ ወላድም በሰላም ተገላግላ ጡት ካጠባች በኋላ ባልተጾመው ቀን ልክ በመጾም ሊያካክሱት ይችላሉ። ፍጹም መጾም የማይችል ደግሞ በጾሙ ቀኖች ልክ የተቸገረውን ጾመኛን ከጾሙ በኋላ በማብላት ማካካስ እንደሚችል መሐመድ-ዓሊ (ዶ/ር) ይገልጻሉ።
የረመዳን ወር
ቅዱስ ቁርኣን መውረድ ከጀመረበትን ቀን ጋር በመያያዙ የቅዱስ ቁርኣን ወር ነው ተብሎ ይጠራል። ቅዱስ ቁርኣንን መቅራትና በትእዛዛቱና በአስተምሮው መመራት የዘወትር ተግባር ቢሆንም በረመዳን ወር ከሌሎች ወሮች በተለየ በግልና በቡድን ይቀራል።
በዚህ የቁርኣን ንባብ በርካታ መለኮታዊ፣ መንፈሳዊ፣ ታሪካዊ፣ ሞራላዊ፣ ህጋዊ ወዘተ… የጸሎት ትምህርቶች እንዲታወሱና እንዲሰርጹ እድል ይፈጥራል።
ጾም ትልቅ ትንሽ፣ ሃብታም ድሃ፣ ጠንካራ ደካማ ሳይለይበት ሁሉም የሚጾሙት በመኾኑ፣ በሁሉም ዘንድ የእኩልነት መንፈስ እንዲሰፍን ያግዛል። ረመዳን ሃብታሙ ድሃውን የሚያስብበት ወር በመኾኑ፣ ይህም ማህበራዊ የመረዳዳት ፋይዳ ያስገኛል።
የረመዳን ወር የሰላም፣ የፍቅር፣ የመተሳሰብ፣ የወንድማማችነት ወዘተ ወርና የእነዚህ እስላማዊ እሴቶች የስልጠና ወር ነው ማለት ይቻላል።
የተራዊህ ሶላት፡-
‹‹ተራዊህ›› የሚለው የአረብኛ ቃል ‹‹ማረፍ›› የሚል ትርጉም አለው። የተራዊህ ሶላት ሲባል አስር ረከዓ ሶላት እያረፉ መስገድ ማለት ነው። ባብዛኛው በረመዳን ወር ምሽት በመስጅድ ካልሆነም በኸለዋ በቡድን ይፈጸማል። በአገራችን በየሁለቱ ረከዓ መካከል በሚኖር የእረፍት ጊዜ በለስላሳ ዜማ ወይም መንዙማ ፈጣሪን ያውቁበታል፣ ነብዩን ይዘክሩበታል፣ ዱዓ ያደርጉበታል።
ፍጡር፡-
በእስልምና ጾመኛን ማስፈጠር ልዩ ቦታና ደረጃ አለው። ያስፈጠረ ሰው በተግባሩ ከፈጣሪው ምንዳ እንደሚቸረው ያምናል። በዚህ መንፈሳዊ ምንዳ የተነሳ ሙስሊሞች ከጎረቤት፣ ከመንገደኛ፣ በተለይም ከችግረኛ ጋር ለማፍጠር ወይም ለማስፈጠር ይጣደፋሉ። በአንድ ማዕድ ዙሪያ ተሰባስበው ቤት ያፈራውን ይቃመሳሉ።
ሶደቃ፡-
ሶደቃ ለራስ፣ በህይወት ለሌለ የቤተሰብ አባል ወይም ለአንድ ለሚያውቁት ሰው ተብሎ ለተቸገሩ የሚሰጥ የምጽዋት አይነት ነው። ኃጢያቶችን ያነጻል፣ ወደፊት ሊመጡ የሚችሉ አደጋዎችን ይታደጋል ተብሎ ይታመናል። በመሆኑም የፈጣሪ ጸጋ ለማግኘት ብዙ ሙስሊሞች የረመዳን ጾምን ይመርጣሉ። የረመዳን ወር ጸጋ በደረጃ የላቀ መሆኑን በማሰብ ሶደቃው በስፋት ይካሄዳል።
ፊዳያ፡-
‹‹ፊዳያ›› ሙስሊሞች በህመም፣ በጉዞ፣ በእርጅና፣ በተለይ ሴቶች በእርግዝና፣ በወሊድና ልጅ በማጥባት ወዘተ ምክንያቶች የረመዳንን ወር በሙሉ ወይም በከፊል መጾም ሳይችሉ ሲቀሩ ላልጾሟቸው ቀኖች የተቸገሩትን የማስፈጠር የማካካሺያ ተግባር ነው።
ከፋራህ፡-
በእስልምና አንድ ሰው በጾም ወቅት የተከለከሉ ሀላልም ሆኑ ሀራም የሆኑ ድርጊቶችን ሲፈጽም ኃጢኣት ይሆኑበታል። ከድርጊቶቹ የሚነፃበት ክፍያ ‹‹ከፋራህ›› ይባላል። የከፋራህ አይነቱና መጠኑ እንደ ድርጊቱ አይነት ይለያያል። ግለሰቡ ከሰራው ኃጢኣቱ ለመንጻት በተከታታይ ስድስት ወር መጾም ይጠበቅበታል። ካልቻለ ስድሳ ችግረኞችን በማብላት ከፈጸመው ኃጢኣት መንጻት ይኖርበታል።
ዘካተል ፍጡር፡-
‹‹ዘካተል ፍጡር›› የረመዳን ወር የፍቺ ክብረ በአልን ለማክበር አቅም የሌላቸው ሰዎች እንደሌሎቹ ተደስተው እንዲውሉ የሚሰጥ ግዴታ የሆነ ክፍያ ነው። ያልከፈለ ሰው የተሟላ ጾም እንደ ጾመ አይቆጠርለትም። ይህ ለተቸገሩት የሚሰጥ ክፍያ ብዙውን ጊዜ በአይነት የሚፈጸም ሲኾን እንደ ሁኔታው በገንዘብ ሊተካም ይችላል። በአይነት ሁለት እፍኝ ስንዴ ይኾናል። በገንዘብ ሲኾን የእህሉ ተመን በረመዳን ወር ገበያ የሽያጭ ዋጋ ይወሰናል።
ዘካተል ፍጡር በቤተሰብ አባላት ብዛት ላይ ያተኩራል። ለምሳሌ በአንድ ቤተሰብ ውስጥ አምስት አባላት ቢኖሩ አምስቱም የቤተሰቡ አባላት እያንዳንዳቸው አስር ኪሎ ስንዴ ወይም የአስር ኪሎ ስንዴ የገበያ ዋጋ ለተቸገሩ ይሰጣሉ።
ኢደል ፍጡር፡-
‹‹ፍጡር›› የሚለው ቃል በመዝገበ ቃላዊ ትርጉሙ ጾም መፍታት ይሆናል። ‹‹ኢደል ፍጡር›› የሚለው ቃል ትርጓሜ ደግሞ የረመዳን ጾም እንዳለቀ ባሉት የሸዋል ወር ሶስት ተከታታይ ቀናት የሚካሄድ የጾም ፍች አከባበር ነው።
ጾሙም ሆነ የጾም ፍች በጨረቃ ዑደት ላይ በመመስረቱ ፍችው በሰላሳኛው ወይም በሀያ ዘጠነኛው ማግስት ሊኾን ይችላል። ከሁለቱ ባንዱ ቀን አንስቶ ለሶስት ተከታታይ ቀናት ኢደል አልፍጡሩ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ይከበራል።
የመጀመሪያው ከጾም ፍቺ ቢያንስ አንድ ቀን አስቀድሞ ለተቸገሩ የጾም ፍቺ የሚሆን ስጦታ ይበረከታል። ስጦታው ዘካተል ፍጡር ይባላል። ዘካተል ፍጥሩ የግዴታ ሲሆን መጠኑ በጊዜው የቤተሰብ አባል ብዛት ይወሰናል። ለምሳሌ የአንድ ሰው የቤተሰብ አባላት አምስት ቢሆኑ ለሁሉም የዘካተል ፍጡር ይከፈላል። ክፍያው በአብዛኛው በአይነት ማለትም ለምግብ አገልግሎት የሚውል የእህል አይነት የሚሰጥ ሲሆን ካልተቻለ በየወቅቱ ዑለሞች በሚያወጡት የወቅቱ የገበያ ተመን መሰረት ክፍያው ወይም ስጦታው በገንዘብ የሚሆንበት አጋጣሚ አለ።
ሁለተኛው የጾም ፍች ከአራቱም ማእዘናት ሙስሊሞች አደባባይ በመገኘት የጾም ፍች ስግደት በጋራ ይፈጽማሉ። ሶስተኛው፣ በሶስቱ ተከታታይ ቀናት ፈጣሪን በማመስገን፣ እርስ በርስ በመጠያየቅና በመዘያየር ሚዛናዊ በሆነ አግባብ ከወትሮው በተለየ መንገድ በደስታና በፍስሃ ማሳለፍ ነው።
በዋዜማ ምሽት ሴቱም ወንዱም ለበዓሉ በድምቀት መከበር የየድርሻቸውን ዝግጅት ያደርጋሉ። የሚበላው የሚጠጣው ይሰናዳል። ሌሊቱ በጸሎት ይታለፋል። ንጋት ላይ ሁሉም ገላውን ተጣጥቦ፣ ጸአዳ ልብስ ለብሶ፣ ህጻን አዛውንት ሳይለይ ለስግደት አቅራቢያው ወደሚገኝ አደባባይ ተክቢራ እያለ ይወጣል።
ከአደባባዩ ስነ ስርአት በኋላ ሁሉም ወደየቤቱ በመመለስ ቀሪ ጊዜውን ከቤተሰቡ፣ ከጎረቤቱ ጋር ቡና በመጠጣት፣ አብሮ በመብላት፣ ዘመድና ወዳጅ በመጠየቅ ያሳልፋል።
እነዚህ ክንውኖች በበእስልምና አስተምህሮ ከሚኖራቸው በረከትና ትሩፋት ባሻገር በሰዎች መካከል ትውውቅ እንዲፈጠር፣ የእርስ በርስ ግንኙነት እንዲዳብርና እንዲጠናከር ትልቅ አቅም የሚፈጥሩ ናቸው።