ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ እያደገ የመጣውን የታዳሽ ኃይል ልማት የሚመጥን ብቁ አመራር ማፍራት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው-የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 1/2016(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ እያደገ የመጣውን የታዳሽ ኃይል ልማት የሚመጥን ብቁ አመራር ማፍራት ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እና የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ።


 

ስምምነቱን የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ፕሬዝዳንት ዛዲግ አብርሃ እና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ስራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ ተፈራርመዋል።

የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ፕሬዝዳንት ዛዲግ አብርሃ በዚሁ ጊዜ አካዳሚው በተለያዩ ዘርፎች ብቁ የሆነ አመራሮችን የማፍራት ስራ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።


 

የዛሬው የመግባቢያ ስምምነትም ተቋማቱ በአመራር ልማት የተሻለ ስኬት ላስመዘገቡ አመራሮች እውቅና መስጠትና ሀሳብ ማመንጫ ማዕከል ማዘጋጀት ላይ በጋራ እንዲሰሩ ያስችላል ብለዋል፡፡

በዘርፉ ብቁ አመራር ማፍራት ከተቋም ባለፈ ለአገር እድገት ሚናው ከፍተኛ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ስራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በአፍሪካ ታዳሽ ሃይል በማመንጨት ቀዳሚ ሀገር ለመሆን እየሰራች መሆኑን ተናግረዋል።

ከዚህ አኳያ በኢትዮጵያ እያደገ የመጣውን የታዳሽ ኃይል ልማት የሚመጥን ብቁ አመራር ማፍራት ተገቢ መሆኑን ጠቅሰው፤ ስምምነቱ ይህን ታሳቢ ያደረገ መሆኑን አንስተዋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም