ቀጥታ፡

 የክልሎች ርዕሳነና ምክትል ርዕሳነ መስተዳድሮች ለኢድ አል ፈጥር በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

ጋምቤላ/ሰመራ/ቦንጋ/ ሆስዕና/ሶዶ ፤ ሚያዚያ 1/2016(ኢዜአ)፡- የጋምቤላ፣ የአፋር፣ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች፣  የማዕከላዊ ኢትዮጵያና የደቡብ ኢትዮጵያ  ክልሎች  ርዕሳነና ምክትል ርዕሳነ መስተዳድሮች ለ1ሺህ 445  የኢድ አል ፈጥር በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ። 

የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ  ባስተላለፉት መልዕክት ፤በረመዳን ወር ህዝበ ሙስሊሙ ማዕድ የማጋራት፣ የመተጋገዝና የመረዳዳት እሴቶችን በተሻለ መልኩ ሲያከናውን መቆየቱን ገልጸዋል።

ህዝበ ሙስሊሙ በጾም ወራት ያሳየውን መተሳሰብ በበዓሉ ወቅትም ሆነ በሌሎቹም ጊዜያት መድገም እንዳለበትም ገልጸዋል።

በበዓል የተቸገሩ ወገኖችን በማገዝ ሰላማዊ በሆነ መልኩ እንዲከበር ማድረግ እንደሚገባም አመልክተዋል።

ህዝበ ሙስሊሙን ጨምሮ መላው የክልሉ ነዋሪ በክልሉ አብሮነትንና አንድነትን በማጠናከር የክልሉን ሰላም  ዘላቂ ለማድረግ ተባብሮ መስራት እንዳለበት በመጥቀስ ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች ለኢድ አል ፈጥር በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በተመሳሳይ የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ ለመላው ህዝበ መስሊም እንኳን ለ1ሺህ 445  የኢድ አል-ፈጥር በዓል አደረሳችሁ የመልካም ምኞታቸውን መልዕክት ሲያስተላለፉ፤ ህዝበ ሙስሊሙ በፆሙ ወቅት ሲያደርግ የቆየውን የበጎ አድራጎት ተግባር በቀጣይም አጠናክሮ መስቀጠል አንዳለበት አመልክተዋል።

ለአገራችን ብሎም ለክልላችን ሰላምና ልማት ላይም ንቁ ተሳታፊ በመሆን የሚጠበቅብንን የዜግነት ግዴታ በአግባቡ መወጣት ይኖርብናል ብለዋል። 

ይህ በእንዲህ እንዳለ ህዝበ ሙስሊሙ በዓሉን በአብሮነት፣ በመረዳዳትና መጠያየቅና መተጋገዝ እንዲያከብር መልዕክት ያስተላለፉት ደግሞ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ ናቸው። 

ይህ ወር  ምዕመኑ ራሱን በጾምና ጸሎት በማትጋት ለአገር ሠላምና ለወገን ደህንነት ሲጸልይ የቆየበት ነው ብለዋል። 

በጾም ወቅት የተቸገሩትን በመርዳትና በማገዝ በአብሮነት እንዳሳለፈው ሁሉ በዓሉንም ደጋፊና ረዳት ከሌላቸው ወገኖቹ ጋር አብሮ እንዲያሳልፍ ጥሪ አቅርበዋል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው በበኩላቸው፤ ሙስሊሙ ማህበረሰብ በረመዳን የፆም ወቅት ያሳየውን አብሮነትና መደጋገፍ በዘላቂነት አጠናክሮ እንዲቀጥል መልዕክት አስተላልፈዋል።

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በዚሁ መልዕክታቸው፤  ሙስሊሙ በጾም ወቅት የተቸገሩ ወገኖቹን በመደገፍ አንድነቱን ለማጠናከርና ለማጎልበት ያበረከተው አስተዋጾ ላቅ ያለ ነው ብለዋል።

በረመዳን የፆም ወቅት ያሳየውን የአብሮነትና የመደጋገፍ ተግባር በዘላቂነት ማስቀጥል እንዳለበትም አመልክተዋል።

በዓሉን ስናከብር ለዘመናት የቆየውን የመቻቻል፣ የአብሮነትና የመደጋገፍ እሴት በማጠናከር ሊሆን ይገባል ሲሉ መልዕክት ያስተላለፉት ደግሞ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ናቸው።

ርዕሰ መስተዳድሩ ፤ በዓሉ ሕዝበ ሙስሊሙ በረመዳን ወር ለሰላም እንዲሁም ፍቅርና አንድነት እንዲበዛ የድርሻውን ሲወጣ መቆየቱን አውስተዋል፡፡ 

በመሆኑም የአብሮነት በዓል የሆነውን የኢድ አል ፈጥር  መተሳሰብን፣ መጠያየቅንና መረዳዳትን በማጎልበት ማክበር ይገባል ብለዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም