ቀጥታ፡

የኢድ አልፈጥር በዓልን ስናከብር የተቸገሩ ወገኖችን በመደገፍ የአብሮነት ባህልን ማጠናከር አለብን -የእምነቱ ተከታዮች

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 1/2016(ኢዜአ)፦ የኢድ አልፈጥር በዓልን ስናከብር  የተቸገሩ ወገኖችን በመደገፍና  የአብሮነት ባህልን በማጠናከር ሊሆን ይገባል ሲሉ የእምነቱ ተከታዮች ገለጹ፡፡

ኢድ አልፈጥር የቅዱሱ ረመዳን ወር ፆም መፍቻ በዓል ነው፡፡  ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ኢድ አልፈጥርን በአደባባይ እና በዋና በዋና ጎዳናዎች በጸሎት እና በስግደት ያከብራሉ፡፡

ኢድ አል ፈጥር በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ከሚከበሩ ታላላቅ በዓላት አንዱ ሲሆን በዓሉ የሚከበረው ወዳጅ ዘመዳሞች በመጠያየቅና ያለው ለሌለው ከጥሪቱ በማካፈል በአብሮነትና በመተዛዘን ነው።

ነገ የሚከበረውን 1 ሺህ 445ኛው የኢድ አል ፈጥር በዓልን አስመልክቶ ኢዜአ የእምነቱን ተከታዮች አነጋግሯል።

አስተያየታቸውን  ከሰጡት የእምነቱ ተከታዮች መካከል ሼህ ኢብራሂም ሁሴን የረመዳን ፆምና የኢድ አልፈጥር መረዳዳትን ፣ መተሳሰብንና አንድነትን የምናሳይባቸው በዓላት ናቸው ብለዋል።  

በዚህም የእምነቱ ተከታዮች በዓሉን ሲያከብሩ የተቸገሩ ወንድምና እህቶቻቸውን ለመርዳት ዘካተር ፊጥር ማውጣት እንደሚገባቸው አሳስበዋል ። 


 

ሌላኛው አስተያየታቸውን የሰጡት የእምነቱ ተከታይ አቶ ከድር ሁሴን በበኩላቸው የረመዳን ፆምን የእምነቱ አስተምህሮ የሚያዘውን ሁሉ በመፈጸም እያሳለፉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

እስልምና ሰላም ፣ ፍቅር ፣ መረዳዳትና መቻቻል መሆኑን በመግለፅ የእምነቱ ተከታዮች የኢድ በዓልን  ሲያከብሩ የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳት፣ የታመሙትን በመጠየቅና የመደጋገፍ ባህልን በማጠናከር መሆን እንዳለበት ተናግረዋል። 

የመረዳዳትና የመደጋገፍ ባህሉን በረመዳን ፆምና በኢድ አልፈጥር በዓል ብቻ ሳይሆን የሁልጊዜ ተግባራችን በማድረግ  አጠናክረን  እንቀጥላለንም ብለዋል።

በዓሉን ስናከብር ቂምና ጥላቻን በማስወገድ ፍቅርንና ሰላምን በማጎልበትና አብሮ የመኖር ባህልን በማዳበር መሆን እንደሚገባም ገልጸዋል።  

 
 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም