ታላቁ የህዳሴ ግድብ ለቀጣናው የሚኖረውን ጉልህ ጠቀሜታ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማስገንዘብ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ስራዎችን አጠናክረን እንቀጥላለን- የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበር - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ የህዳሴ ግድብ ለቀጣናው የሚኖረውን ጉልህ ጠቀሜታ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማስገንዘብ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ስራዎችን አጠናክረን እንቀጥላለን- የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበር
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 1/2016(ኢዜአ)፦ታላቁ የህዳሴ ግድብ ለቀጣናው የሚኖረውን ጉልህ ጠቀሜታ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማስገንዘብ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ስራዎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበር ገለጸ።
የግንባታ መሰረቱ መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም የተጀመረው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በመንግስት የአመራር ቁርጠኝነትና በኢትዮጵያውያን የተባበረ ጥረት የግንባታ አፈጻጸሙ 95 ነጥብ 8 በመቶ ደርሷል፡፡
የግድቡ ግንባታ ባለፈባቸው ምዕራፎች ሁሉ አንዳንድ አካላት ግድቡ በታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት ላይ ጉዳት ያደርሳል የሚል መሰረተ ቢስ መረጃን በማሰራጨት ጫናዎችን ሲያደርጉና ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ለማደናገር ሲሞክሩ ነበር።
ኢትዮጵያ የዓባይ ወንዝን በፍትሐዊነት እና በጋራ የመልማት መርህን መሰረት በማድረግ ለመጠቀም ግድቡን እየገነባች ሲሆን፥ ይህንንም ለዓለም ለማስገንዘብ ተደጋጋሚ ጥረቶችን አድርጋለች።
ዳያስፖራው ማህበረሰብም ለግድቡ መሳካት በገንዘብ ድጋፍ እና በፐብሊክ ዲፕሎማሲ ጉልህ ሚና እያበረከተ ስለመሆኑ ይነሳል።
በሚኖርባቸው ሀገራትም የኢትዮጵያን እውነታና የግድቡን ቀጣናዊ ሚና ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በማስረዳት በኩል በርካታ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበር ስራ አስፈጻሚና የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አብርሃም ጥላሁን ለኢዜአ እንደገለጹት፥ ግድቡ አሁን ለደረሰበት ምዕራፍ በውጭ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ቦንድ መግዛትን ጨምሮ የተለያየ አበርክቶ ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡
ግድቡ "ዳግማዊ ዓድዋ" ነው የሚሉት አቶ አብርሃም፥ ግድቡን በተመለከተ የነበሩ ጫናዎችን ለመመከት እና ቀጣናዊ ጠቀሜታውን ለማሳወቅ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ስራዎች በስፋት ይከናወኑ እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡
ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ጸጋዋን ተጠቅማ ከመልማት ውጪ ሌሎችን የመጉዳት አላማ እንደሌላት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የማስገንዘብ ስራዎችን በተከታታይ መከናወናቸውን በመጥቀስ።
በቀጣይም የኢትዮጵያን የመልማት መብትና የፕሮጀክቱን ቀጣናዊ ሁለንተናዊ ጠቀሜታ ለዓለም የማሳወቅ ጥረቶችን አጠናክረን እንቀጥላለን ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበር የቦርድ አማካሪ አቶ ኤርሚያስ መኮንን በበኩላቸው፤ በተለያየ የዓለም ክፍል የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለሀገራቸው ሰላምና ልማት በጎ ሚና እየተወጡ ነው ብለዋል።
ለአብነትም ለህዳሴ ግድብ ግንባታ የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ፣ ስለ ግድቡ እውነተኛ መረጃዎችን ለዓለም በማሳወቅ እና የሀሰት መረጃዎችን በመቀልበስ የላቀ አበርክቶ እንዳላቸው አውስተዋል።
በቀጣይም ግድቡ እስከሚጠናቀቅ ድረስ የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያደርጉና ለሀገራቸው ዘላቂ ጥቅም መከበር ዲፕሎማሲያዊ ስራዎችን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቁመዋል።
የታላቁ የህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት መረጃ እንደሚያሳየው ኢትዮጵያውያን ባለፉት 13 ዓመታት ለግድቡ ግንባታ ከ19 ቢሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ድጋፍ አድርገዋል።