ቀጥታ፡

ለሕዳሴ ግድብ ግንባታ የምናደርገው ድጋፍ ይቀጥላል - የካፋ ዞን ነዋሪዎች

ቦንጋ ፤ ሚያዚያ 1/2016(ኢዜአ)፦  ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የካፋ ዞን ነዋሪዎች ገለፁ።

በኢትዮጵያውያን ገንዘብ አስተዋጽኦ ግንባታው እየተከናወነ ያለው የሕዳሴው ግድብ የመሠረት ድንጋይ ከተቀመጠ 13ኛ ዓመቱን አስቆጥሯል።

በመላው የአገሪቱ ክፍሎች  የሚኖሩ ዜጎችም የግንባታ ሥራው 95 ከመቶ የደረሰውን ግድብ እስኪጠናቀቅ ድረስ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ በመግለጽ ላይ ናቸው።

ኢዜአ ያነጋገራቸው በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የካፋ ዞን ነዋሪዎችም የሕዳሴ ግድብ ግንባታው እስኪጠናቀቅ ድረስ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ነው የገለጹት።

የቦንጋ ከተማ ነዋሪዋ ወይዘሮ መቅደስ ለይኩን በግድቡ ግንባታ ሂደት ከደመወዛቸው ቦንድ በመግዛት ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ገልጸዋል።

አሁንም ግንባታው ሙሉ ለሙሉ እስኪጠናቀቅ ድረስ ድጋፋቸው አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

በንግድ ሥራ የሚተዳደሩት ሌላኛው የቦንጋ ከተማ ነዋሪ አቶ ጌታቸው ወልደሰንበት በበኩላቸው ለግድቡ ግንበታ በእርሳቸውና በቤተሰባቸው ስም በአምስት ዙር ከ25 ሺህ ብር በላይ የሚገመት ቦንድ መግዛታቸውን ገልጸዋል።

ግድቡ ለአገር ኢኮኖሚም ሆነ ለዜጎች ብልፅግና የሚኖረው አስተዋፅኦ የጎላ በመሆኑ ለግንባታው ማስፈጸሚያ የሚሆን ቦንድ በመግዛት ድጋፋቸውን እንደሚያጠናክሩ አረጋግጠዋል።

በዞኑ የጊምቦ ወረዳ ኡፋ ከተማ ነዋሪ አቶ እንዳለ አደቆ ኢትዮጵያውያንን ከዳር እስከ ዳር ላንቀሳቀሰው፣ የአንድነታችንና የአብሮነታችን ማህተም ለሆነው የሕዳሴው ግድብ አስተዋጽኦ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ይገልጻሉ።

"ግድቡ አሁን የደረሰበት ደረጃ ላይ በመድረሱ ደስተኛ በመሆኔ ግንባታውን ለማጠናቀቅ ድጋፌን እቀጥላለሁ" ብለዋል።

ከስደት ተመልሰው ነዋሪነታቸውን በቦንጋ ከተማ ያደረጉት ወይዘሮ አዚዛ አብዱልቃድር ከነበሩበት አገር  ድጋፍ ሲያደርጉ እንደነበረ አስታውሰዋል።

"ግድቡ ተጠናቆ ለልማት ሲውል ያለውን ጠቀሜታ በመረዳት በቀጣይም የግድቡ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድረስ ድጋፌን እቀጥላለሁ" በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም